
ባሕር ዳር: የካቲት 2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለዓመታት የበይነ መረብ የቪዲዮ ተግባቦት (video calling) አማራጭ ኾኖ የቆየው እና በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች የነበሩትን ስካይፕ በመጭው ግንቦት ወር ጀምሮ ሊዘጋ መኾኑን ባለቤት ኩባንያው ማይክሮሶፍት ገለጿል፡፡
ከዚህ ቀደም በይነ መረብን በመጠቀም ከቤተሰብ እና ጓደኛ ጋር ርቀት ሳይበግረው በነፃ መጠቀም የሚያስችል ዝነኛ ዌብሳይት ነበር ሲል ዘገባው አመላክቷል፡፡
ስካይፕ እንዲህ አይነት አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ብቸኛ አማራጭ ባይኾንም ሰዎች በኮምፒውተሮቻቸው አማካኝነት በነፃ የድምፅ እና ምስል መልዕክት በቀጥታ እንዲለዋወጡ የሚያደርግ በመኾኑ ተመራጭ ነበር ተብሏል፡፡
በመጭው ግንቦት ወር ይዘጋል ከመባሉ ጋር ተያይዞ ተጠቃሚዎች የግንኙነት ታሪኮቻቸው እና አድራሻቸው ሳይጠፋ ከስካይፕ ወደ ሌላኛው የማይክሮሶፍት የግንኙነት አማራጭ ማይክሮሶፍት ቲም መዞር የሚችሉ መኾኑን በይፋዊ የኤክስ የማኅበራዊ ገጽ ኩባንያው ማሳወቁን የቢቢሲ ዘገባ አስነብቧል፡፡
እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ2003 አገልግሎት መስጠት የጀመረውን ይህ የግንኙነት አማራጭ ማይክሮሶፍት በ2011ዓ.ም በ 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ሲገዛው በወቅቱ በጣም ትልቅ ወጭ የተደረገበት ግብይት ነበር፡፡
ኩባንያው እንደገለጸው ስካይፕ ከኤክስ ቦክስ እና ዊንዶውስ ምርቶች ጋር ተሳስሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ የስካይፕን የመዘጋት ዜና የሰሙ ከበፊት ጀምሮ ተጠቃሚ የኾኑ ደንበኞች ስካይፕ በሕይወታቸው የነበረውን ትውስታ እና በጎ ተጽዕኖ ገልጸዋል፡፡
ስለመዘጋቱ ዜና በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ የተሰማቸውን ያጋሩ ተጠቃሚዎች በርካታ አይረሴ ትውስታዎችን ከወዳጆቻቸው ጋር በስካይፕ ይጋሩ ነበር። የዘመናዊ የእጅ ስልክ እና ዋትስአፕ ከመፈጠራቸው በፊት ለብዙዎች ደስታን ይፈጥር የነበረ ትልቅ ፈጠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ቀስ በቀስ የፌስቡክ እና ዋትስአፕ ዝና እየናኘ ሲሄድ ስካይፕ ግን እያሽቆለቆለ ሄደ፡፡ በ2017 ዓ.ም ኩባንያው አዲስ ማሻሻያን ጨምሮ በአዲስ መልክ ብቅ ብሎ ነበር፡፡ ቢኾንም ተጠቃሚዎች ብዙም ደስተኛ አልነበሩም፡፡
ይህን ተከትሎ በሰኔ ወር 2021ዓ.ም ሊዘጋ ይችላል የሚል መላምት መሰንዘር ተጀምሮ ነበር፡፡ ከዚያም ራሱ ማይክሮሶፍት ስካይፕን ሊያቆም እንደሚችል የሚጠቁም ነገር በምርቱ ላይ አሳዬ፡፡
ዊንዶውስ 11 ምርቱን ሲተዋወቅ ከ11 በፊት በነበሩት ዊንዶውስ ላይ ይካተት የነበረውን ስካይፕን እንዲቀር አደረገ፡፡ አሁን ደግሞ በይፋ ይዘጋል የሚል መረጃን አጋርቷል፡፡ ለዚህም ኩባንያው በሌላኛው ቲም በተሰኘ የግንኙነት አማራጩ ላይ ትኩረት አድርጎ አገልግሎት መስጠት ስለፈለገ ነው የሚል ምክንያት ማጋራቱን የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል፡፡
ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ የቴክኖሎጂ አማራጮች በፍጥነት እያደጉ እና እየዘመኑ መምጣቱ በነባሮቹ ላይ በዚህ ልክ ተፅዕኖን የማሳደር አቅማቸው ከፍ እያለ መጥቷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!