“የዓድዋ ድል የጥንት አባቶቻችን ጀግንነትና ለሀገር ያላቸውን ፍቅር ያስመሰከሩበት ድል ነው” የአማራ ክልል መንግሥት

41

ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ለዓድዋ ድል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። የክልሉ መንግሥት ሙሉ መልዕክቱ:- እንኳን ለ129ኛዉ የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ! “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል!”

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበርና የሕዝቦቿን አንድነት ለማስጠበቅ በተለያዩ ዘመናት ወረራ የፈፀሙባትን የውጪ ወራሪ ኃይሎች በመፋለም በበርካታ አውደ ውጊያዎች ተደጋጋሚ የሆኑ ሀገርን ያፀኑና ያስቀጠሉ ታሪካዊ ድሎችን ተጎናፅፋለች፡፡ ከእነዚህ ድሎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሀገራችን ብቻ ሣይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል የሆነው የዓድዋ ድል ነው፡፡

ከዛሬ 129 ዓመት በፊት አያቶቻችን ባርነትንና ቅኝ ተገዥነትን እምቢ አሻፈረኝ ብለው የቋንቋ፤ የሃይማኖት፣ የፆታና የባህል ልዩነት ሳይበግራቸው ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት በዓድዋ ምድር በፍፁም ጀግንነትና በሀገር ፍቅር ስሜት ተፋልመው ድል በማድረግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አስከብረዋል፡፡ ሀገርና ሀገረ መንግሥት አስቀጥለዋል፡፡

በጦርነቱም ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት የአርሶ አደር አንድ ሺህ በላይ ኪሎ ሜትሮችን በባዶ እግሩ ተጉዞ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነ ሠራዊትን፣ በመረጃ፣ በዲፕሎማሲና በፖለቲካ ጥበብ የሰለጠነውንና ዘመናዊ የጦር መሳሪያን እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጣሊያን ቅኝ ገዥ ወራሪ ጦር ህልም ከንቱ በማድረግ ከአንድ ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የካቲት 23/1888 ዓ.ም ዓድዋ ላይ ድል ተቀዳጅቷል፡፡

በዓድዋ የጦር አውድማ ለእናት ሀገራቸው ነፃነትና ክብር ሕይወታቸውን ለመስጠት ያልሳሱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በአፍሪካ ምድር በክቡር ደማቸው አፍሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው የዛሬ ነፃነትን ሚስጥር በዓድዋ ተራሮች ላይ ጽፈዋል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአፍሪካና በመላው ዓለም ደምቃና ከብራ ከፍ ብላ ከመታየቷ ባሻገር በልጆቿ ተጋድሎና ቆራጥነት በዓለም የነፃነት ምድር፣ የጥቁር ሕዝቦች የአይበገሬነት ተምሳሌት ሆና ቀጥላለች፡፡

የዓድዋ ድል የጥንት አባቶቻችን ጀግንነትና ለሀገር ያላቸውን ፍቅር ያስመሰከሩበት ድል ሲሆን ሀገራችንን ከነጮች ቅኝ አገዛዝ በመታደግ በዐቀለም አቀፍ መድረክ እንድትታወቅና እንድትከበር ምክንያት የኾነ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም መመስረትና መጎልበት አስተዋፅኦ ያበረከተ፣ ሀገራችን ሉዓላዊት ሀገር መዃኗን ያረጋገጠ ነው፡፡

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን የትብብር፣ የአንድነት፣ የኩራትና የክብር ምንጭ የሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን እና ክብርን ያተረፈልን ልዩ የአባቶቻችን የመስዋዕትነት በረከት ነው፡፡ ለሰው ልጆች ክብር ፤ ለሰብአዊ መብት ታጋዮች እንዲሁም ለጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ የወኔ ስንቅ የሆነና መነቃቃትን የፈጠረ ታላቅና አንፀባራቂ ድል ነው፡፡ ድሉ በመላው ኢትዮጵያዊያን በየዓመቱ የሚከበር ሲኾን ዛሬም የካቲት 23/2017 ዓ.ም ለአንድ መቶ ሃያ ዘጠነኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

በመሆኑም በአሉን ስናከብር የዓድዋ ድል በዓለም አቀፍ ታሪክ ውስጥ የፈጠረውን ልዩና አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ በመከተል የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን ታላቅ የሀገር ፍቅር፣ ነፃነትና አንድነት በተግባር ማሳየት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህን ለማሳየት ደግሞ አባቶቻችን የጦር ግንባር መስዕዋት ሆነው ያስረከቡንን ነጻነት፣ ሀገር ክብርና ዝና ለመጠበቅ፤ በተሰማራንበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ጠንክረን በመሥራት ከድህነት የተላቀቀችና የበለጸገች ኢትዮጵያን መገንባት ይጠበቅብናል፡፡

“ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል!”
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
የካቲት 23 ቀን 2017 ዓ.ም
ባሕርዳር

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article129ኛው የዓድዋ ድል በዓል ” ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ መልእክት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዜየም በድምቀት እየተከበረ ነው።
Next articleበአንድነት ከማሰባሰብ እስከ ድል አድራጊነት የዘለቀው የእምዬ ምኒልክ አዋጅ!