
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመከላከያ ሚኒስቴር ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል እንኳን በሠላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል። የዓድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያዊያን የጀግንነት ታሪክ የሚዘከርበት አያቶቻችን ዘመን ባልዘመነበት በያኔው ዘመን ፋሽስት ኢጣሊያንን በጦር በጎራዴ ታዋግተው ያሸነፉበት የእኛነታችን ማረጋገጫ ነው ብሏል።
ዓድዋ የአንድነታችን የኅብረታችን ማሳያ ነው፣ ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪውን ያሸነፉበት ብቻ ሳይኾን ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት መሆኑን የገለፁበት በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ጀግኖቻችን እየዘከርን ኅብረታችንን በሚያጎሉ ነገሮች ላይ በማተኮር ብቻ ሊሆን ይገባል ነው ያለው።
የዓድዋ ድል ለትውልዱ ጀግንነትን፤ አብሮነትን፤ ማሸነፍን ፤ነፃነትን እና አንድነትን ያሥተማረ የጥቁር ሕዝቦች የድል በዓል ነው ብሏል። በመሆኑም ለሀገራችን ሠላም ዘብ እንደቆምነው ሁሉ በልማቱ መስክም አሻራችንን በማሣረፍ እና የልማት ተሳታፊ በመኾን የኢትዮጵያን ዕድገት ማረጋገጥ ይገባናል ነው ያለው።
የመከላከያ ሚኒስቴር የዓድዋ ድል በዓል አከባበርን በባለቤትነትና በማስተባበር እንዲመራ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ከተቋቋመው ሀገራዊ ኮሚቴ ጋር በመኾን የዓድዋ ድል በዓልን ከባለ ድርሻ አካላት እና ከመላው ሕዝባችን ጋር በመሆን እያከበረ ይገኛል ብሏል።
ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከአያቶቻችን ከአባቶቻችን የተረከብናትን ኢትዮጵያ ማንነቷን አሥከብረን፣ ሠላሟን አሥጠብቀን፣ በጀግንነቷ ፀንታ እንድትዘልቅ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መኾን፣ ለሠላም እና ለልማት ዕድገታችን መታተር ይገባናል ነው ያለው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!