
ባሕር ዳር: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፉ ናቸው፡፡ እነዚህ በሽታዎች በእድሜ መጨመር፣ በፈጣን የከተሞች መስፋፋት እና ጤናማ ባልኾኑ የአኗኗር ዘይቤዎች ምክንያት የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ለሞት እየዳረጉ እንደኾነ ይገለጻል። በኢትዮጵያም የማኅበረሰብ ፈተና ናቸው።
በሀገራችን ብዙ ዓይነት ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ቢኖሩም የልብ ሕመም፣ የደም ግፊት፣ የኩላሊት ሕመም፣ ስትሮክ፣ ካንሰር እና የስኳር ሕመም በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸዉ፡፡በእነዚህ በሽታዎች የተጠቁት እና እየተጠቁት ያሉት ወገኖች በርካቶች ናቸው። ስማቸውን መጠቀስ ያልፈለጉ በጉልምስና እድሜ ክልል ያሉ የኩላሊት እጥበት ታካሚ እንደሚሉት ለረጅም ዓመታት የስኳር በሽታ ተጠቂ በመኾን መድኃኒት ይወስዱ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
ጎልማሳው እንደሚሉት የስኳር በሽታ መድኃኒቱን ተከታትለው ወስደዋል። ጫት ይቅሙ፣ አልኮል ይጠጡ እና ትምባሆ ያጨሱ ስለነበር ሕመሙ መሻሻል አላሳየም። በእነዚህ የተሳሳቱ አካሄዶች ከስኳር ሕመሙ በተጨማሪ ለልብ ሕመም፣ለደም ግፊት እና ለኩላሊት በሽታ በቀላሉ እንደተጋለጡ ተናግረዋል። አሁን የኩላሊት እጥበት ጀምረው በከፍተኛ የጤና ችግር ላይ እንደሚገኙ ገልጸውልናል፡፡
ሌላው አቶ አክሊሉ ተገኝ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ከሁለት ዓመት በፊት ጠዋት ከመኝታቸው ሲነሱ ቀኝ እጅና እግራቸው አልታዘዝ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡ አቶ አክሊሉ ወደ ሕክምና በመሄድ ሲታዩ የደም ግፊት መጠናቸው ጨምሯል፡፡ ለረጅም ጊዜ ባደረጉት የሕክምና ክትትል ጤንነታቸው ወደ ነበረበት ተመልሷል ብለዋል። አሁን ላይ አመጋገቤን በማስተካከል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማዘውተር እና ከአልኮል መጠጥ በመራቅ በጥሩ ጤንነት ላይ እገኛለሁ ነው ያሉት፡፡ በየጊዜውም የደም ግፊት መጠናቸውን እየተለኩ ራሳቸውን እንደሚቆጣጠሩ ገልጸውልናል፡፡
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ኦፊሰር ዶክተር ቴዎድሮስ ጌታቸው ለአብዛኛዎቹ ተላላፊ ላልኾኑ በሽታዎች አጋላጭ መንስኤዎች ትምባሆ ማጨስ፣ አብዝቶ የአልኮል መጠጥ መጠጣት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ጤናማ ያልኾነ የአመጋገብ ሥርዓት መኾኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶክተሩ ገለፃ እነዚህ በሽታዎች ሊሻሻሉ የማይችሉ ወይም የማይቀየሩ አጋላጭ ሁኔታዎች እና ሊሻሻሉ የሚችሉ ወይም ሊቀየሩ የሚችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች ተብለዉ በሁለት ይከፈላሉ፡፡
ሊሻሻሉ የማይችሉ ወይም የማይቀየሩ አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት ከዕድሜ እና ዘር ጋር ተያይዘዉ የሚመጡ ናቸው። እነዚህን በሽታዎች ማሻሻል እንደማይቻል ነገር ግን በአመጋገብ፣ በአካል እንቅስቃሴ እና በሕክምና ክትትል ባለበት መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ሊሻሻሉ የሚችሉ ወይም ልንከላከላቸዉ የሚችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች የምንላቸዉን ደግሞ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ትምባሆ ባለማጨስ፣ በሚያጨሱ ሰዎች አካባቢ ባለመገኘት፣ አልኮል ባለመጠቀም እና ጤናማ ያልኾኑ የአመጋገብ ሁኔታዎችን በማስወገድ መቀነስ እና መቆጣጠር እንደሚቻል ነው የገለጹት።
ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በየጊዜው በጤና ተቋማት በመደበኛነት አጠቃላይ ምርመራ በማድረግ የጤንነት ሁኔታውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ልማዱን ማዳበር እንዳለበትም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!