ባዮሜትሪክ የደኅንነት ሥርዓት

54

ባሕር ዳር: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባዮሜትሪክ ከሁለት የግሪክ ቃል የተዋቀረ ነው። ባዮ ማለት ሕይዎት ሲኾን ሜትሪክ ማለት ደግሞ ልኬታ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ሲዋሃዱ ልዩ ተፈጥሯዊ የመለያ ባሕርይ ልኬታን የሚገልጽ ነው፡፡ ባዮሜትሪክስ ሰዎች ያላቸውን ልዩ አካላዊ መለያ የሚመረምር እና ልዩ የሚያደርገውን ገጽታ በመለካት እና በማመሳከር ተግባራዊ የሚያደርግ የደኅንነት አማራጭ ነው፡፡

ሰዎች በፊታቸው ገጽታ፣ በገጽ ቀለማቸው፣ በእጅ እና ዐይን አሻራቸው እንዲኹም በድምጻቸው በሚኖራቸው ልዩነት አንዱን ከሌላው መለያ ኾኖ ያገለግላል፡፡ በዋናነት የአንድን ሰው ልዩ ማንነት በመለየት ለዛ ሰው ብቻ የኾነ መገለጫ ኾኖ የሚያገለግል ነው፡፡ በተጨማሪም በአንድ ዘመናዊ ሥርዓት ይህን ዘዴ በመጠቀም አንድን አገልግሎት ለማግኘት ወይም ለመፍቀድ የይለፍ መቆጣጠሪያ በመኾንም ይሠራል፡፡

ለምሳሌ ከተፈቀደላቸው ሰዎች ውጭ እንዲገቡ የሚከለከልበት ጠንካራ የደኅንነት ቁጥጥር የሚፈልጉ ቦታዎች ላይ የተፈቀደላቸው ሰዎች ብቻ በዐይን አሻራቸው፣ በፊት ገጻቸው አልያም በእጅ አሻራቸው እንዲገቡ ለመፍቀድ ይጠቅማል፡፡ ባዮሜትሪክስን ቀለል ባለመንገድ ለመረዳት በዘመናዊ የእጅ ስልኮች ላይ ያለውን የአሻራ እና የፊት ገጽታ ልዩ መለያን መውሰድ ይቻላል፡፡ ስልኮቻችንን ለመቆለፍ ከሌሎች የተለመዱ የደኅንነት መጠበቂያ መንገዶች ውጭ አሻራን እንጠቀማለን፡፡ ከዚህ ቀደም ካስገባነው የእጅ አሻራ ጋር በማዛመድ እና የተሳሳቱትን በመመርመር ስልካችን በእኛ መለያ ብቻ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲኾን ያደርጋል፡፡

ይህ የደኅንነት አማራጭ የተለያዩ ድርጅቶች ያላቸውን መገልገያ መሳሪያ እና አገልግሎቶች ደኅንነት ለመጠበቅ እና ማን መገልገያዎቹን እና አገልግሎቶች መጠቀም ይችላል የሚለውን የሚለዩበት ስለኾነ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ የባዮሜትሪክ የደኅንነት አማራጭን ተግባራዊ ለማድረግ የባዮሜትሪክስ ናሙና መውሰጃ መሳሪያ (reader or scanning device)፣ የተወሰደውን ናሙና ወደ ዲጂታል መረጃ የሚቀይር መተግበሪያ እና የባዮሜትሪክስ መረጃዎችን በአግባቡ ሰንዶ የሚያስቀምጥ ቋት (database) ያስፈልጋል፡፡

የደኅንነት ሥርዓቱ ናሙናን ይወስዳል፣ የወሰደውን ናሙና ወደ ዲጂታል መረጃ ይቀይራል፣ ከዚህ በፊት ከገባ ናሙና ጋር ያነጻጽራል፤ በመጨረሻም ትክክለኛ መኾኑን እና አለመኾኑን ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ሂደት ለተለያዩ አገልግሎቶች የሰዎችን ማንነት ለይቶ የመፍቀድ እና የመከልከል ሥራን ይሠራል፡፡
በፊደላት፣ በቁጥሮች እና ልዩ ምልክቶች የምንጠቀማቸው የይለፍ ቃላት ከሚሰጧቸው አገልግሎቶች በተሻለ ለመረጃ ጥቃት እና መጭበርበር የማያጋልጥ አማራጭ ነው፡፡

በተጨማሪም ናሙናዎች ብዙ ቦታ የሚይዙ ባለመኾናቸው ሀብት ቆጣቢም ናቸው፡፡ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በፍጥነት እያደገ መምጣት ደግሞ በጣም ብዙ መጠን ያለውን የባዮሜትሪክስ መረጃ በአጭር ጊዜ ተንትኖ ለማረጋገጥ የሚያስችል አማራጭ ስላለው የተጭበረበሩ ማንነቶች እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡
ምንጭ

#https://www.techtarget.com/searchse…/definition/biometrics
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዳኝነት እና ፍትሕ ሥርዓቱን ማሻሻያ ድጋፍ ላደረጉ አካላት የእውቅና መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው።
Next articleለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ማዘጋጀቱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ገለጸ።