ሰውን ተክቶ የሚሠራው አዲስ ቴክኖሎጂ!

32

ባሕር ዳር: ጥር 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሜሪካዊው የሰው ሠራሽ አስተውሎት የምርምር ተቋም ኦፕን ኤ.አይ በይነመረብ ላይ የሰው ልጅ ሊያከናውን የሚችላቸውን ተግባራት ተክቶ መሥራት የሚችል አዲስ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ይፋ አድርጓል። ቴክኖሎጂው ኦፕሬተር ተብሎ ይጠራል። የታዘዘውን ተግባር ለማከናወን ድረ ገጽ ላይ ያሉ ይዘቶችን ያስሳል።

የተግባቦት ቁልፎችን ይጫናል (clicking Keys)፣ የገጾችን ሙሉ ይዘት ለማየት ወደ ላይ እና ወደታች ገጹን ያንቀሳቅሳል (scrolling) አስፈላጊ ሲኾን በመተየብ የድረ ገጹን የግንኙነት አማራጭ ተጠቅሞ የተሰጠውን ሥራ በአግባቡ ይሠራል። ኦፕን ኤ.አይ በድረ ገጹ ባወጣው መረጃ መሠረት ይህ የሰው ሠራሽ አስተውሎት አማራጭ ገና ሙሉ ሂደቱን ያልተሻገረ እና ከተጠቃሚው የሚሰጠውን ግብረ መልስ በመሠብሠብ የተሻለ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ለሙከራ የተለቀቀ መኾኑን ገልጿል።

ድርጅቱ በአይነቱ ለየት ያለው ይህ ቴክኖሎጂ ያለእኛ ጣልቃ ገብነት ራሱን ችሎ ሥራን መሥራት የሚችል የመጀመሪያ ፈጠራ እንደኾነም አሳውቋል። ኦፐሬተር የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ድረ ገጹ ላይ ባወጣው ጽሑፍ አሰልቺ ሊባሉ የሚችሉ ሥራዎችን እንዲሠራልን በማዘዝ ብቻ በፈለግነው መንገድ እንደሚያግዘን አሳውቋል።

ቅጾችን መሙላት፣ መደብሮች ላይ የሚገዙ ዝርዝሮችን ማዘዝ እና በመዝናኛው ዘርፍ ደግሞ የተለያዩ አዝናኝ ጉዳዮችን ለማዘጋጀት ያገለግላል። በሰው ልጅ የዕለት ከዕለት የሕይዎት እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ የሥራ ጫናዎችን ከማገዝ ባለፈ የንግድ ተቋማት በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዙ የንግድ ግንኙነቶችን የሚያደርጉበት አዲስ መንገድ የሚፈጥርም ጭምር ነው።

አሁን ላይ ኦፕሬተር ዶት ቻትጂፒቲ ዶት ኮም (Operator.chatgpt.com) ድረ ገጽ ላይ በመግባት የሚገኝ ሲኾን ገና የምርቱን ውጤታማነት ለመገምገም የተለቀቀ በመኾኑ በአሜሪካ ግዛቶች እንዲሞከር ነው የተለቀቀው። በተሻለ መንገድ አገልግሎቱን ከቻትጂፒቲ ጋር አስተሳሰሮ ለማቅረብ ዓላማ ይዞ እየሠራ መኾኑን የድርጅቱ ድረ ገጽ አስነብቧል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleመንገዶች በጋ ከክረምት እንዲያገለግሉ ኾነው እየተገነቡ ነው።
Next articleወጣቶች በሰላም ግንባታ ላይ አተኩረው እንዲሠሩ ተጠየቀ።