ከጥራት ደረጃ በታች የሆኑ ከ2 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ታገዱ፡፡

146

አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃን ያላሟሉ ከ2 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መታገዳቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለፉት 9 ወራት አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው የገቢ ምርቶች ላይ ባካሄደው የጥራት ቁጥጥር ከ2 ሺህ 500 ሜትሪክ ቶን በላይ ከደረጃ በታች በመሆናቸው ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ታግደዋል፡፡

በቁጥጥሩ ከታገዱት የገቢ ምርቶች ውስጥ 2 ሺህ 304 ነጥብ 95 ሜትሪክ ቶን ጥቅል ብረት፣ 28 ነጥብ 7 ሜትሪክ ቶን የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ 180 ካርቶን ሳሙና፣ 142 ካርቶን በፀሐይ ብርሃን የሚሠራ የእጅ ባትሪ፣ 150 ካርቶን የኤሌክትሪክ ገመድ እና 43 ነጥብ 22 ሜቴሪክ ቶን የቆርቆሮ መስሪያ ጥሬ ዕቃ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም 272 ጥቅል የአርማታ ብረት፣ 19 ሺህ 770 ጀሪካን ፓልም የምግብ ዘይት፣ 2 ሺህ 934 ፍሬ የውኃ ፓምፕ፣ 875 ካርቶን ባትሪ ድንጋይ፣ የታሸጉ ምግቦችና ሌሎችም የገቢ ምርቶች በቁጥጥሩ ወቅት ከጥራት መስፈርት በታቸ ሆነው በመገኘታቸው ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ እንዳይገቡ መደረጉን ነው ሚኒስቴሩ ያመለከተው፡፡

በተደረገውም ቁጥጥር ምርቶቹ ሀገር ውስጥ ቢገቡ በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሱትን የጤና፣ የደኅንነትና የጥቅም ጉዳት ማስቀረት መቻሉን ሚኒስሩ አስገንዝቧል፡፡

ምንጭ፡- የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

Previous articleየጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት 9 ወራት 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የሚገመት ኮንትሮባንድ መያዙ አስታውቀዋል፡፡
Next article“በቀውስ ወቅት ተግባቦት የሚሠራጭ መረጃ ዓላማው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ፍርሃት ወይም መዘናጋት እንዳይፈጠር ማድረግ ነው፡፡” አደም ጫኔ (ዶክተር)