
ባሕር ዳር: ጥር 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የሠባር አፅሙ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል እየተከበረ ነው። የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ባለፈ ለባሕር ዳር ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
በበዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ ሊቃውንት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ምዕምናን ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር እና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብርሃም አባቶቻችን እና እናቶቻችን ይህን ታላቅ በዓል በጣና ሐይቅ ላይ ያከብሩት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል ብለዋል።
በመካከል በልዩ ልዩ ምክንያቶች በዓሉ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ውስጥ ብቻ እንዲከበር ኾኖ እንደነበርም አስታውሰዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ በጣና ሐይቅ ላይ እየተከበረ ነው ብለዋል።
በዓሉ ወደ ቀደመ ክብሩ እንዲመለስ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ብፁዕነታቸው ታሪክ ጠባቂ እና አስጠባቂ አያሳጠን ነው ያሉት። ታሪክን መጠበቅ ያስመሰግናልም ብለዋል።
ይሄን ታላቅ በዓል ስናከብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ዓይነት የእግዚአብሔር ባለሟል እንደ ነበር፣ ለሃይማኖቱ ያለውን ጽናት፣ የሃይማኖት ብርታትን ለትውልዱ ያስተማረበትን እንዘክራለን ነው ያሉት። እግዚአብሔር ለስሙ የሚንበረከኩለትን፣ እርሱን የሚያምኑትን ያድናቸዋል ብለዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሃይማኖቱ ወደ ኋላ የማይል መኾኑንም አንስተዋል። ከእግዚአብሔር ቃል ያፈነገጡ ነገሥታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸሙት ተግባር ዘግናኝ መኾኑን ያነሱት ብፁዕነታቸው የነገሥታቱን ድርጊት ክፉ ሥራ ሁልጊዜም ሲያስወቅስ እንደሚኖር እንማርበታለን ነው ያሉት። የቅዱስ ጊዮርጊስን ሰማዕትነት እና የእግዚአብሔርን ባለሟልነት ዕፅዋት ሳይቀሩ የመሰከሩለት መኾኑንም ገልጸዋል።
ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጽናትን እና ብርታትን እንማር ብለዋል። ነገሥታቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በሥልጣን፣ በገንዘብ አባብለውታል፣ እርሱ ግን የዚህ ዓለም ሥልጣን እና ቁሳቁስ የማይጠቅም መኾኑን የተረዳ ነውና አምላኩን እና ጌታውን በምንም እንደማይክደው ሳይፈራና ሳያፍር ነገራቸው ነው ያሉት ብፁዕነታቸው።
የጸና የማያልፍ ክብር፣ የማይጠፋ ስም ይሰጠዋል ያሉት ብፁዕነታቸው ክርስቲያኖች በሙሉ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሃይማኖታችን እንጽና ብለዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ያስተማረው ጸንቶ ማለፍን መኾኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክን፣ ባሕል እና ሃይማኖትን በሚገባ ይዛ የዘለቀች፣ ሀገርን ያወረሰች መኾኗንም ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያኗን ማክበር እንደሚገባም አሳስበዋል። የእያንዳንዱ ሃይማኖት መከበር እና መጠበቅ እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው በአንድ ላይ መኖር፣ በአንድ ላይ መሥራት፣ መረዳዳትን ነው ብለዋል። ስድብ እና ጥላቻ የሰይጣናዊ ባሕሪ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው በዚህ ዘመን ተሳዳቢዎች መብዛታቸውንም ገልጸዋል።
ትዕግስትን ገንዘብ እናድርግም ብለዋል። ፍቅር እና ሰላምን እንሰብካለን ያሉት ብፁዕነታቸው በሕግ እና በሥርዓት እንማማራለን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!