ጤናማ የሕይዎት ዘይቤን በመከተል እና መደበኛ የጤና ክትትል በማድረግ የጀርባ ሕመምን መከላከል ይገባል፡፡

37

ደብረ ማርቆስ: ጥር 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጀርባ ሕመም በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚከሰት እና በዕለት ከዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል የጤና ችግር ነው፡፡ የጀርባ ሕመም ከተለያዩ የሥነ ሕዝብ እና የአኗኗር ዘይቤዎች ጋር የሚያያዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት እየታየ ያለ የጤና ችግር መኾኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና በደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጭንቅላት፣ የኅብረ ሰረሰር እና የነርቭ ሐኪም ዶክተር መሠረት ዘውዴ ከአንገት ጀምሮ እስከ መቀመጫ ድረስ የሚሰማ ማንኛውም ሕመም የጀርባ ሕመም ተብሎ እንደሚጠራ ገልጸዋል፡፡ አከርካሪን ጨምሮ በጀርባ ጡንቻ ላይ የሚገኙ መገጣጠሚያዎች እና የነርቭ ዘንጎች ላይ የሕመም ስሜት ሲከሰት የጀርባ ሕመም ምልክት ሊኾን ስለሚችል ችግሩን በጥንቃቄ መከታተል እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ከዓለማችን ሕዝብ ከ80 እስከ 85 በመቶ የሚኾነው በሕይዎት ዘመኑ አንዴ የጀርባ ሕመም ሊያጋጥመው እንደሚችል የገለጹት ባለሙያው የጡንቻ መሳሳብ እና መሰል በቀላሉ ሊታከሙ የሚችሉ ምክንያቶች ለጀርባ ሕመም መንስኤዎች ሊኾኑ ይችላሉ ብለዋል፡፡ እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ወደ ጀርባ የተዛመተ ካንሰር፣ ቲቪ፣ የዲስክ መንሸራተት፣ የነርቭ ዘንጎች ላይ የሚደርስ ጫና እና መሰል ምልክቶች ለጀርባ ሕመም አጋላጭ በመኾናቸው እስከ ቀዶ ጥገና የሚደረስ ሕክምና ሊደረግ እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

ከአንድ ወር በታች የሚቆዩ የጀርባ ሕመሞች በፊዚዮቴራፒ ሕክምና፣ የሕይዎት ዘይቤን በማሻሻል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ መከላከል እንደሚቻልም አስገንዝበዋል። ከሦስት ወራት በላይ የቆዬ የጀርባ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ግን በሕክምና የሚታዘዙ መድኃኒቶችን መውሰድ እና የሕክምና ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው ዶክተር መሠረት አብራርተዋል፡፡

የታወቀ የካንሰር ሕመም ያለባቸው፣ ከፍተኛ የክብደት መቀነስ፣ የመውደቅ አደጋ ያጋጠማቸው እና ክፍተኛ ሙቀት የሚሰማቸው ሰዎች የጀርባ ሕመም የሚያስከትለውን ውስብስብ ችግር ለመከላከል የሕክምና ባለሙያዎችን ሊያማክሩ ይገባልም ብለዋል።

ባለሙያው እንደሚሉት አብዛኞቹ ቀላል የጀርባ ሕመሞች ያለሕክምና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን በመከተል የሚስተካከሉ ናቸው ነው ያሉት፡፡ ነገርግን ከባድ የጀርባ ሕመሞች እስከ ቀዶ ሕክምና እና የነርቭ ሕክምና ድረስ የዘለቀ ከፍተኛ ክትትል የሚጠይቁ መኾናቸውንም አስረድተዋል፡፡

ኅብረተሰቡ ጤናማ የሕይዎት ዘይቤን ከመከተል ባለፈ መደበኛ የጤና ክትትል በማድረግ የጀርባ ሕመምን መከላከል እንደሚገባው ነው ዶክተር መሠረት የመከሩት፡፡

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የማይሠራ ጉልበት፣ የማይለማ መሬት አይኖርም!”
Next articleረቂቅ አዋጁ የመሬት አሥተዳደር እና አጠቃቀምን በማዘመን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።