
ባሕር ዳር: ጥር 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥምቀት በዓል መሠረቱ ሃይማኖት ቢኾንም እንኳ ባሕላዊ እሴቱም ተወዳጅ እና ቀልብ ሳቢ ነው፡፡ ጥምቀት ላይ ውበት ሞልቶ ይፈሳል። ማራኪ አለባበስ እና የሞቀ ጭፈራ በጥምቀት በዓል የሚጠበቅ ነው፡፡
ጥምቀት ሃይማኖታዊ ክዋኔን ማሳለጫ ብቻ ሳይኾን የማኅበራዊ ሕይወት መሠረት የሚጣልበትም ነው። በጥምቀት ደስታ፣ እልልታ ፣ ትዳር፣ ፍቅር እና ውበት አጀንዳ ይኾናሉ፡፡ በዚህ ወቅት ታድያ ከቀኑ ጋር የተያያዙ ሥነ ቃሎች እና ግጥሞች ሌላው ትኩረትን የሚስቡ ናቸው።
በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቋንቋ ልማት ባለሙያዉ ቢተው ህሊና ሥነ ቃሎች እና ግጥሞች በሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ወቅት ተግባር ላይ የሚውሉ የሕዝብ ሃብቶች ስለመኾናቸው ይናገራሉ።
ደራሲያቸው እና ማን እንደፈጠራቸው ለማወቅ የሚያዳግቱት ቃላዊ ግጥሞች ከትውልድ ወደ ትውልድ በመነገር የሚሸጋገሩ ቃላዊ ፈጠራ ናቸው ይላሉ። ሃብትነታቸው ደግሞ የሕዝብ እንደኾኑ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ቢተው ገለጻ ሥነ ቃሎች ኃይል አላቸው። ሰዎች በሥነ ቃሎች አማካኝነት መልዕክት ያስተላልፍሉ። ብሶታቸውን ሥነ ቃልን እንደ መሣሪያ በመጠቀም ያንጎራጉሩበታል፤ ደስታቸውንም በሥነ ቃል አጋዥነት ይፈነድቁበታል ብለዋል።
ሥነ ቃሎች ማኅበረሰባዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ፋይዳቸው የጎላ ነው። ሃይማኖታዊ ፋይዳቸውም በእጅጉ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ሥነ ቃል መሠረታዊ ባህሪው ክዋኔ ነው ያሉት አቶ ቢተው ተለዋዋጭነትም ሌላው መለያው እንደኾነ አብራርተዋል።
ባንድ ዘመን በማኅበረሰቡ ዘንድ አገልግሎት ላይ የነበረ ሥነ ቃል በባለቤቱ ሕዝብ አማካኝነት በሌላ ጊዜ ተለውጦ ሊገኝ ይችላል ነው ያሉት።ለአብነት ይሉና ባንድ ወቅት:-
“ትመጫለሽ ብየ ሳይ ማዶ ሳይ ማዶ፣
የልጅነት አይኔ ሟሟ እንደ በረዶ” የሚለው ቃላዊ ግጥም በሌላ ወቅት ቀልጦ እንደ በረዶ ሊኾን ይችላል ነው ያሉት። በሥነ ቃል ውበት ይገለጻል፤ በሥነ ቃል ብሶት ይነገራል፤ በሥነ ቃል ትንቢት ይታለማል፤ በሥነ ቃል እምነት ይታጀባል። ሥነ ቃል ፍቅር ይገለጽበታል፤ አድናቆት ይተላለፍበታል። ሰዎች በሥነ ቃል ይግባባሉ። በሥነ ቃልም ይተረጓጎማሉ፤ ብቻ ሥነ ቃል ከማኅበረሰቡ የሚፈልቅ፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚኖር የወል ሀብት ነው።
በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሥነ ቃል አገልግሎት ላይ ከሚውልባቸው ሁነቶች ውስጥ ታድያ የጥምቀት ሰሞን አንዱ ነው። ጥምቀት በኢትዮጵያ ሲከበር ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባሕላዊ ክዋኔዎች ይናፈቃሉ፡፡ የወይዛዝርቱ ‹እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ› የጸጉር አሠራር እና አበጣጠር፣ የጎበዞች አለባበስ እና አጊያጊያጥ፣ ከሰው ሁሉ ልቆ እስክስታ ለመውረድ እና በተለየ ቃና ፈጣሪውን ለማስደሰት ያለው ውድድር ልዩ ድባብ ያለው ነው። በለስ የቀናው ደግሞ የሕይወት አጋሩን ይዞ የመመለስ ዕድልም ሊገጥመው ይችላል፡፡ ብቻ ጥምቀት አንዳች ልዩ ትርጉም ያለው ነው።
በጥምቀት በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚዜሙ የምሥጋና እና የውዳሴ ግጥሞችም አሉ፡፡ “ለጥምቀት ያልኾነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚለው ቃላዊ ነገራ በዚህ ወቅት ተግባር ላይ ይውላል።
በቃል የተነገረው በተግባር ይተረጎምና የጥምቀት ዕለት የማይወጣው የክት ልብስ ባደባባይ ይውላል። ሥነ ቃሉ ከወግ በዘለለ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ለጥምቀት በዓል የሚሰጠው ክብር የሚንጸባረቅበትም ነው። በጥምቀት ዕለት ከሚነገሩ ግጥሞች ውስጥ:-
👉ነይ ነይ እምዬ ማርያም (2)
እቴ ባንዱ ልጅ በመድኃኔዓለም።
👉ከርሞ እመጣለሁ ብላሃለች (2)
እድሜዋን በቁና ለክተውናለች?
👉አደራ አደራ መድኃኒዓለም
ምን አልባት ምን አልባት ሰው አይኾነው የለም።
👉ከርሞ እንገናኝ ለዓመት
አንተም ደህና ብትኾን እኛም ባንሞት።
👉እኔስ ለዚህች ዓለም እሳሳለሁ።
አምና የነበሩት ሲቀሩ አይቻለሁ።
👉የተልባ አበባ ነው ገላዬ
ዘወር ብዬ ባየው አፈር በኋላዬ።
👉ኧረ አዘቀዘች ፀሐይ
የቆንጆቹን አንገት ልታይ።
👉አንሳ አንሳ አይደለም ወይ ኋላማ
ሰው ከሞተ ወዲያ ከተገነዛማ።
👉እጣን እጣን ሸተተኝ መሬቱ
እናቴ እመቤቴ ያደረችበቱ።
👉ኧረ እንግዲህ ዓለም ለምኔ
ለረፋድ ጎዳና ለቀን ተኩል እድሜ።
👉አረ ተወኝ ተወኝ ከርሞ ባይ
በሰኔ በግንቦት ሞት አይመጣም ወይ?
👉ዓመት ደግመኝ ጌታዬ
ከርሞስ ብትደግም እኔ ምን ተዳዬ። እና ሌሎች የወል ቃላዊ የሕዝብ ሀብቶች የጥምቀት ዕለት ይዘወተራሉ። በሚያምር ዜማ ሲዜሙ፣ እልልታው እና ጭብጨባው ሲያስተገባ ልዩ ቃና ይፈጥራል። ጥምቀትም ይናፈቃል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!