ከአዘዞ አርበኞች አደባባይ -ጎንደር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ገለጸ።

36

ባሕር ዳር፡ ጥር 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አጠቃላይ 12 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነውን ከአዘዞ አርበኞች አደባባይ – ጎንደር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በቅርቡ ለማጠናቀቅ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የፌደራል መንግሥት በመደበው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው ይኽ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በሌላ የሀገር በቀል የሥራ ተቋራጭ አማካኝነት ግንባታው ሲከናወን ቆይቶ ከአፈጻጸም ውስንነት ጋር በተያያዘ ውሉ መቋረጡ ይታወቃል።

የፕሮጀክቱን ቀሪ ሥራዎች በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንዲቻል በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የጎንደር መንገድ ጥገና ዲስትሪክት ግንባታውን ተረክቦ እየሠራ ይገኛል። 21 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ በመገንባት ላይ በሚገኘው በዚሁ ፕሮጀክት አብዛኛው የስትራክቸር እና ተጨማሪ ዋና ዋና የፕሮጀክቱ ሥራዎች ተጠናቅቀዋል።

አሁን ላይ የአስፋልት ማንጠፍ ሥራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንገዱ የቀኝ አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ አስፋልት የማንጠፍ ሥራ ተጠናቅቋል። የግራው አቅጣጫ ደግሞ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ሲቀር የአስፋልት ንጣፍ ተደርጎለታል፡፡ የመንገዱ የግንባታ ሂደት በመዘግየቱ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ለትራንስፖርት መስተጓጎል ችግር ሲዳረጉ ነበር። አሁን ላይ የግንባታ ሂደቱ እየተፋጠነ በመኾኑ ችግሩ እየተቀረፈ ይገኛል፡፡

መንገዱ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረውን የከተማውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ችግር የሚያቃልል ከመኾኑም ባሻገር ከሰሜን ጎንደር ወደ መተማ እና ሌሎች የማዕከላዊ ጎንደር አካባቢዎች የሚደረገውን የትራንስፖርት ፍሰት ያሳልጣል።

ዲስትሪክቱ አሁን ላይ ከዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪ 700 ሜትር የጎንደር ከተማ አስፋልት ሥራ እና ሌሎች ተጨማሪ ተግባራትን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር መረጃ ይጠቁማል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጥምቀት ለጎንደር ከማኅበራዊ ትስስሯ ባሻገር የምጣኔ ሃብት ምንጯም ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኛው
Next articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሕር ዳር ዲስትሪክት የደንበኞች አገልሎት ወርን እያከበረ ነው።