የወባ ሥርጭት አሳሳቢነት

36

ባሕር ዳር: ጥር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ201 ዓ.ም ጀምሮ የወባ በሽታ እየጨመረ እንደመጣ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል። በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የወባ ሕሙማን የተመዘገቡ ሲኾን በዚህ ዓመት ደግሞ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል።

ደቡብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር እና አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ ሥርጭት ካለባቸው አካባቢዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በተለይም ደግሞ 40 ወረዳዎች የክልሉን 70 በመቶ የወባ ሥርጭት ይይዛሉ ተብሏል። ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ከሚታይባቸው አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ የአዊ ብሄረሰብ አሥተዳደር አንዱ ነው። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከሰኔ መጨረሻ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 176 ሺህ 219 ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ መረጃ ያሳያል። በተለይም ደግሞ አየሁ ጓጉሳ፣ ጓንጓ፣ ዚገም፣ ቻግኒ እና ጃዊ ወረዳዎች የዞኑን አጠቃላይ የወባ ሥርጭት ከ82 በመቶ በላይ ይሸፍናሉ። የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ደግሞ በቀዳሚነት ተቀምጧል።

በወረዳው አዘና ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት ይሻሙሽ አሥረስ እንዳሉት በአካባቢው የወባ ታማሚዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከነበረው ጨምሯል ብለዋል። ማኅበረሰቡ በባለሙያዎች ድጋፍ በመታገዝ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ቢሠራም ሥርጭቱ አሁንም የማኅበረሰብ ሥጋት ኾኖ ቀጥሏል። በወባ በሽታ የተጠቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች በመንግሥት ጤና ተቋማት በቂ መድኃኒት ስለማያገኙ በግል የጤና ተቋማት እንዲገዙ ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ ለከፍተኛ ወጭ እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል ብለዋል።

ሌላኛው በቀበሌው ነዋሪ የኾኑት አቶ አሥራት በሬ በአካባቢው የወባ ሥርጭቱ ባልተለመደ ሁኔታ በመጨመሩ የጤና ተቋማት በሕሙማን ተጨናንቀው መመልከታቸውን ተናግረዋል። በየጊዜው በባለሙያ የታገዘ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ቢኾንም በሽታው ሥጋት መኾኑን ነው ያነሱት። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተመስገን ፈንታሁን እንዳሉት በወረዳው በአራት ወር ብቻ 40 ሺህ ሰዎች በወባ ተጠቅተዋል። ይህም በ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ በወባ ከተያዙት ሕሙማን እጥፍ መኾኑን ነው የገለጹት።

የአየር ንብረት መቀያየር፣ በተማሏ መንገድ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ አለመሥራት፣ የመከላከል ሥራን በሙሉ አቅም አለመሥራት፣ ወባማ በኾኑ ሁሉም አካባቢዎች ርጭት አለማካሄድ፣ ሕሙማን የታዘዘላቸውን መድኃኒት በአግባቡ አለመውሰድ ለሥርጭቱ እንደምክንያት አሥቀምጠዋል። ሥርጭቱን ለመከላከል መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ጭምር ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል። የምርምር ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች የበሽታውን ሥርጭት ምክንያት እና የቀጣይ መፍትሔ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንደሚገባ መክረዋል።

በአማራ ክልል ከሐምሌ 1/2016 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ 2017 ዓ. ም ድረስ 3 ሚሊዮን 112 ሺህ 772 ሰዎች የወባ ምርመራ ማድረጋቸውን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልላዊ የወባ መከላከል ግብረ ኀይል ሰብሳቢ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) ገልጸዋል። ከተመረመሩት ውስጥ 1 ሚሊዮን 315 ሺህ 970 የሚኾኑት የወባ በሽታ ሕሙማን ናቸው።

በተለይም ደግሞ በክልሉ 40 ወረዳዎች የክልሉን 70 በመቶ የወባ ሥርጭት ይሸፍናሉ ተብሏል። እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ ያለው የወባ ሥርጭት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 64 በመቶ መጨመሩንም ነው ያነሱት። የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ለይቶ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በትኩረት አለመሥራት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የመኝታ አጎበር በወቅቱ አለመተካቱ እና ማኅበረሰቡም የተሰጠውን የመኝታ አጎበር በአግባቡ አለመጠቀም ለወባ በሽታ ስርጭት መጨመር እንደ ዋና ምክንያት ተቀምጠዋል።

በኬሚካል እጥረት ምክንያት የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት የሚካሄድባቸው ቀበሌዎች ቁጥር መቀነስ፣ ወደ ወባማ አካባቢዎች የሚደረግ የሰዎች እንቅስቃሴ እና ከፍተኛ የኾነ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ በክልሉ መኖር ለሥርጭቱ ሌላው ምክንያት ኾኖ ተቀምጧል። ሥርጭቱን ለመከላከል ባለፉት ወራት ከፍተኛ የወባ ጫና ባለባቸው 27 ወረዳዎች በሚገኙ 233 ቀበሌዎች የቤት ውስጥ የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭትም ተካሂዷል።

ከጥቅምት 15/2017 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ዘወትር አርብ “የአርብ ጠንካራ እጆች የወባ በሽታን ይገታሉ” በሚል መሪ መልዕክት ለተከታታይ 11 ሳምንታት ክልላዊ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ዘመቻ ሲሠራ ቆይቷል። የወባ በሽታን ለመቆጣጠር በማኅበረሰቡ ተሳትፎ እና ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል። ጤና ተቋማትም የወባ መከላከልን መደበኛ ሥራ አድርገው በትኩረት እንዲሠሩም አሳስበዋል። በክልሉ ሁሉም ወባማ ቀበሌዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን የማዳፈን እና የማጽዳት ሥራ እንዲሠሩም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሀገርን እና ወገንን መውጋት ትርፉ ውርደት እንጂ ክብር ሊኾን አይችልም” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleከ451 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠበሠበ።