
ባሕር ዳር: ጥር 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለአንድ ትልቅ ሕዝብ እና ትልቅ የሚዲያ ተቋም በየትኛውም ቦታ ኾኖ መረጃ ማድረስ የሚቻልበት አማራጭ ማፈላለግ ግድ የኾነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ይህን በመረዳት አሚኮ ዘመኑ የደረሰበትን ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ የቀጥታ ስርጭት ማስተላለፊያ ኦቢ ቫን ገዝቶ የበለጠ ተደራሽ ለመኾን ዛሬ በይፋ አስመርቋል።
ከዚህ በፊት ከስቱዲዮ ውጭ ይተላለፉ የነበሩ ሁነቶችን ለሕዝብ ለማድረስ በጣም አድካሚ የኾነ ሂደትን ማለፍ አስገዳጅ ነበር። የተለያዩ መሳሪያዎችን ማጓጓዝ እና መገጣጠም የግድ ይል ነበር። ዛሬ በይፋ የተመረቀው ይህ ቴክኖሎጂ ይህን ሁሉ ችግር የሚቀርፍ፣ ፍጥነት፣ ጥራትን እና የሃብት ብክነትን የሚቆጥብ አማራጭ ነው።
ፕሮዳክሽን መቆጣጠሪያ ክፍል፣ የድምጽ መቆጣጠሪያ ክፍል እና ሴንትራል አፖራተስ የሚባሉ ክፍሎች ያሉት ነው – ይህ ኦቢ ቫን። የፕሮዳክሽን መቆጣጠሪያ ክፍሉ የሥርጭት ዳይሬክተሮች፣ የስዊች ባለሙያዎች፣ የዜና ጽሑፎችን የሚያሥተዳደሩ ባለሙያዎች፣ የትዕይንት ምልሰት ወይም ሪፕሌይ መሳሪያዎችን የሚቆጣጠሩ እና ሌሎችም ባለሙያዎች ሥራዎችን የሚከውኑበት ክፍል ነው። በተጨማሪም የተለያዩ የትዕይንት መቆጣጠሪያ መስኮቶች እንዲሁም የተመጣጠነ የአየር ሁኔታ እንዲኖር የሚያደርግ ኤር ኮንዲሽኒንግ ሥርዓት አለው።
የድምጽ መቆጣጠሪያ ክፍሉ ድምጽን መቆጣጠር የሚያስችል ሚክሰር፣ ስፒከሮችን እና ሌሎችንም ሥርዓቶች አቅፎ የያዘ ነው። የኃይል አቅርቦት ሥርዓት መቆጣጠሪያ ክፍሉ አቅርቦቱን፣ የኃይል አማራጭን እና ምጣኔውን የተመለከቱ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ መሳሪያዎች የሚተዳደሩበት ነው።
የካሜራ መቆጣጠሪያ ክፍሉ ደግሞ ሌላኛው የኦቢ ቫኑ አካል ነው። 8 እና ከዛ በላይ ካሜራዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ክፍል ነው።
ቴክኖሎጂው ለየት የሚያደረገው አሁን ካለው በላይ ደረጃውን ማሳደግ የሚቻልበት አማራጭ ያለው መኾኑ እና የታጠቃቸው መሳሪያዎች ጥራት ከፍ ያለ በመኾኑ ነው። በሀገር ውስጥ ካሉት ኦቢ ቫኖች ለየት የሚያደርገው ልዩ ነገሩ የተለያዩ የደኅንነት መቆጣጠሪያ ሴንሰሮች የተገጠሙለት በመኾኑ ነው፡፡
ሴንሰሮቹ ከመንቀሳቀሱ በፊት መደረግ ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን ቀድሞ በመረዳት መረጃ ይሰጣል። የኃይል ፍስቱን መመጠን እና መቆጣጠር የሚያስትል ሥርዓትም ያለው ቀላል እና ቀልጣፋ ቴክኖሎጂ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!