ቻት ጂፒቲ ምንድን ነው ? (ሳይቴክ ዘመነኛ)

100

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቻት ጂፒቲ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን የተላበሰ የቋንቋ መዋቅርን ተረድቶ ሰዎች ለሚሰጡት የጽሑፍ ትዕዛዝ ምላሽ የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ነው።

ቻት ጂፒቲ ቻት እና ጂፒቲ ከሚባሉ ሁለት ቃላት የተዋቀረ ነው። ቻት የሚለው የቴክኖሎጂውን ከሰው ጋር በጽሑፍ የመግባባት ሂደት ለመግለጽ ሲኾን ጂፒቲ ደግሞ ጄነሬቲቭ ፕሪትሬንድ ትራንስፎርመር ወይም ቀድሞ በተደረገለት የልምምድ ሂደት የጽሑፍ መመሪያን ወይም ትዕዛዝን ወደ ውጤት መቀየር የሚያስችልን ቴክኖሎጂ ለመግለጽ ነው።

ቻት ጂፒቲ በልምምድ ሂደት በጣም ብዙ የጽሑፍ መረጃዎችን፣ ትዕዛዛትን እና መልሳቸውን፣ ሰዋሰውን እና መሰል ነገሮችን ሊረዳ የሚችልበትን ሁኔታ ስለሚያሳልፍ ውጤት የሚያመነጨውም ያንን መሠረት በማድረግ ነው።

ኦፕን ኤ .አይ በመባል በሚጠራው የአሜሪካው የሰው ሠራሽ አስተውሎት የምርምር ተቋም የተፈጠረው ቻት ጂፒቲ አሁን ባለንበት ዘመን ድንቅ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ከሚባሉት ውስጥ በጉልህ የሚጠቀስ ነው።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት እጅግ ሰፊ የሳይንስ ዘርፍ ሲኾን በሥሩ ያለው ቻት ጂፒቲ ላይ ለመድረስ ማሽን ለርኒንግ፣ ጄነሬቲቭ ኤ.አይ እና ለርጅ ላንጉዊጅ ሞዴል የሚባሉ ክፍሎችን አልፈን እንመጣለን ።

ቻት ጁፒቲ በጄነሬቲቭ ኤ.አይ ውስጥ የሚመደብ የሰው ሠራሽ አስተውሎትን የተላበሰ ውሥብሥብ የቋንቋ መዋቅርን በመረዳት ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ነው።

ቴክኖሎጂው በሚደረግለት የልምምድ ሂደት ላይ ተመስርቶ የሰው ልጅ የሚፈጥረውን አይነት ጽሑፍ መጻፍ፣ ግጥም መግጠም፣ የፕሮግራሚንግ ኮዶችን ማመንጨት እና ምስል መፍጠር ይችላል ።

የሰው ልጅ ከኮምፒውተር ጋር በጽሑፍ እየተግባባ የተለያዩ ተግባራትን ለመሥራት እና ድጋፍ ለማግኘት ይጠቀምበታል። ለመግባባት የምንጠቀመው ግልጽ የጽሑፍ መመሪያ ወይም ትዕዛዝ ፕሮምት ይባላል ።

ቻት ጂፒቲ ዋነኛ ግቡ በፕሮምት ለቀረበለት ጥያቄ የሰው ልጅ ሊሰጠው የሚችለውን አይነት ምላሽ መስጠት ነው። በሞባይል መተግበሪያ እና በዌብ ሳይት አማራጭ ስላለ ይህን ቴክኖሎጂ በቀላሉ መጠቀም ይቻላል።

ቴክኖሎጂው የኢሜሎችን ቢጋር እና ሌሎችንም ጽሑፎች መጻፍ፣ መተርጎም እና ይዘት ማመንጨት ይችላል። በመኾኑም የዲጂታል ሺያጭ ሠራተኞች ፣ ጦማሮች እና የፊልም ጸሐፊዎች ይዘት ለማመንጨት ይጠቀሙበታል። የንግድ ተቋማት በደንበኞቻቸው ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመለየት እና የሥራ ጫናን ለመቀነስ ይገለገሉበታል።

የሶፍትዌር ልማት ባለሙያዎችም እንደ አጋዥ አድርገው ይጠቀሙበታል ። በተጨማሪም ለመረጃ ትንተና ሥራም አገልግሎት ላይ ይውላል ።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ መልእክት!
Next articleኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ።