የተዘነጋው የጤና ችግር!

28

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ አውሮፖውያኑ የዘመን አቆጣጠር የ2023 የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ውስጥ እንዳለባቸው አስነብቧል። በዚሁ ዓመት 630 ሺህ ሰዎች ከኤች አይቪ ጋር በተያያዘ ሕይዎታቸው ያልፋል፤ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚኾኑ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል ይላል።

በዓለም ላይ ከፍተኛውን ሥርጭት የሚይዘው አሕጉር ደግሞ አፍሪካ ሲኾን በተለይም ከሰሀራ በታች የሚገኙ እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጀሪያ፣ ሌሴቶ እና ቦትስዋና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ። በኢትዮጵያ አዲስ አበባ፣ ጋምቤላ፣ ሀረር እና ድሬዳዋ የኤች አይቪ ሥርጭቱ ከፍተኛ መኾኑን በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ እና የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዴስክ ኀላፊ ሀብታሙ ካሳ በቅርቡ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በተሠራው ሥራ በኢትዮጵያ የኤች አይቪ ሥርጭት ምጣኔ በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ2010 ከነበረው 1 ነጥብ 26 ወደ ዜሮ ነጥብ 87 መቀነስ ተችሏል። እንደ ሀገር ሥርጭቱ ከ1 በመቶ በታች ቢኾንም ሥርጭቱ አሁንም ከክልል ክልል፣ ከከተማ ከተማ ልዩነት እንዳለው መረጃው ያሳያል።

በተለይም ደግሞ በስድስት ክልሎች የሥርጭት ምጣኔው አሁንም ከ1 በመቶ በላይ ነው። ሥርጭቱ አዲስ አበባ እና ጋምቤላ 3 ነጥብ 2 በመቶ፣ ሀረር 2 ነጥብ 7 በመቶ፣ ድሬ ዳዋ 2 ነጥብ 5 በመቶ፣ ትግራይ 1 ነጥብ 2 በመቶ፣ አማራ ክልል ደግሞ 1 ነጥብ 1 በመቶ ነው። በገጠር ዜሮ ነጥብ 4፣ በከተማ ደግሞ 2 ነጥብ 9 በመቶ የስርጭት መጠን ያለው መኾኑን ነው መረጃው የሚያሳየው። በኢትዮጵያ በአንድ ዓመት በኤች አይቪ ከሚያዘው 7 ሺህ 442 ሰዎች ውስጥ ወጣቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት ከአሚኮ ጋር በየበራቸው ቆይታ የኤች አይ ቪ በሽታ የክልሉ ችግር መኾኑን ገልጸዋል። በሽታው በሀገሪቱ የነጻ ሕክምና ከታወጀ ጀምሮ የመከላከል ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጫና መቀነስ የተቻለ ቢኾንም የመከላከል ሥራው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የኤች አይቪ ሥርጭትን ለመቀነስ መከላከል፣ ተጠቂዎችን በመለየት መመርመር እና በምርመራ የተለዩትን ማከም ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። በመከላከል ሥራው ደግሞ ለሦሰት ጉዳዮች ትኩረት ተሠጥቷል። የማኅበረሰብ ክፍልን መሠረት ያደረገ የመከላከል ሥራ አንዱ ነው። ሴተኛ አዳሪዎች፣ የትዳር አጋራቸው የሞቱባቸው፣ የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ ተንቀሳቃሽ ሠራተኞች፣ የሕግ ታራሚዎች የመሳሰሉ ወደ ስምንት የሚደርሱ ለበሽታው “ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው” ተብለው የተለዩ ቡድኖች የመከላከል እና ምርመራ ሥራ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል።

ሌላኛው የመልካ ምድር አቀማመጥ የበሽታ ሥርጭትን መሠረት ያደረገ የመከላከል ሥራ ነው። በክልሉ 72 ወረዳዎች ከፍተኛ፣ 102 ወረዳዎች ደግሞ በመካከለኛ ደረጃ የኤች አይቪ ሥርጭት ጫና ያለባቸው ተብለው በተለዩት ወረዳዎች በልዩ ትኩረት የመከላከል ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ሌላው ትኩረት የተሠጠው የምርመራ አገልግሎት ነው። በክልሉ በተደረገው ጥናት መሠረት 173 ሺህ 414 የኅብረተሰብ ክፍሎች ኤች አይቪ በደማቸው ይገኝባቸዋል ተብሎ ይታመናል። ከዚህ ውስጥ 160 ሺህ 357 በምርመራ የተገኘ ነው። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ለ155 ሺህ 782 ተጠቂዎች ሕክምና እየተሠጠ ነው። ከተጠቂዎች ውስጥ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 30 የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ከ60 በመቶ በላይ የሚኾኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል።

በግጭት ምክንያት ወደ ተለያየ ቦታ ፍልሰት መኖሩ እና ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለበሽታው ሥርጭት እንደ ምክንያት ተቀምጠዋል። በሽታውን ለመቀነስ መመርመር ብቻ ሳይኾን መከላከል ላይም ትኩረት ተደርጎ ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

በቂ የኤች.አይ.ቪ ኪት በፌዴራል አለመቅረብ፣ ክልል ላይ የደረሰውን ወደ ተቋማት በወቅቱ የማጓጓዝ እና ተቋማት ላይ የደረሰውን ደግሞ የአጠቃቀም ችግር መኖር አሁንም ፈታኝ መኾናቸውን አንስተዋል።

ከዚህ ችግር ለመውጣት የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራት እና ሁሉም ማኅበረሰብ ኀላፊነትን በመውሰድ ድርሻን መወጣት ያስፈልጋል ተብሏል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በትንሽ መዋጮ ሕይዎትን መታደግ አስችሏል” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleየሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ለድርጅቶቹ ሃብት የመፍጠር ነጻነትን የሰጠ ነው።