የደኅንነት ካሜራ

59

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 17/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደኅንነት ካሜራ በአንድ አካባቢ ያለን እንቅስቃሴ ለመከታተል የሚተከል የቁጥጥር ሥርዓት አካል ሲኾን አሁናዊ ሁኔታን የሚያሳዩ እና እያንዳንዱን ትዕይንት ቀርጸው እንዲያስቀምጡ ከመረጃ ቋት ጋር የተሳሰሩ ካሜራዎች ናቸው። የደኅንነት ካሜራዎች በተለያዩ ቦታዎች ሊተገበሩ ይችላሉ። በንግድ ተቋማት ሊደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን፣ የደንበኞችን እና የሠራተኞችን ባሕርይ እና ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ለመቆጣጠር እንዲሁም መረጃ ለመያዝ ይጠቀሙባቸዋል።

በመኖሪያ ቤቶች ላይ ደግሞ ንብረትን ለመቆጣጠር፣ ያልታወቁ ወይም እንዲገቡ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ወደ ግቢ ለመግባት ሲሞክሩ የምንከታተልበት እና መረጃ የምንይዝበት ነው። በትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተሽከርካሪ ፍሰትን ለማሥተዳደር እና ለመቆጣጠር ትልቅ ሚናን ይጫወታል። የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር ይጠቅማል።

የሽያጭ መደብሮች የደኅንነት ካሜራዎችን በመትከል የእጅ አመል ያለባቸውን በመግታት፣ የሽያጭ ሠራተኞችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር እና አጠቃላይ የመደብሩን ኹኔታ በመቅረጽ መረጃ ይሰጣል። ሰዎች የሚሠበሠቡባቸው እና የሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች እና መንገዶች ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ወንጀሎችን በመቆጣጠር የደኅንነት ስጋትን ይቀንሳል።

በትምህርት፣ በጤና እና ሌሎችም ተቋማት ያለን ወጭ እና ገቢ የሰዎች እንቅስቃሴ በመቆጣጠር አካባቢያዊ ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ያደርጋል። ይህ ቴክኖሎጂ በሀገራችን በትላልቅ ተቋማት እና አልፎ አልፎ ደግሞ በግለሰቦች ቤትም የምናስተውለው ሲኾን አሁን ላይ በከተሞች ዝማኔ ወይም ከተሞችን ስማርት በማድረግ ሂደት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በባሕር ዳር ከተማም የከተማዋን ልማት ለማፋጠን የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ተጀምሯል። ፕሮጀክቱ ቀልጣፋ አገልግሎቶችን መስጠት፣ ደኅንነትን መጠበቅ፣ ብልሹ አሠራርን ማስወገድ፣ ምቹ እና ሳቢ ከተማ መፍጠር የሚል ዓላማ ያለው ነው። ደኅንነትን ከመጠበቅ አኳያ በሂደት ላይ ያለውም የደኅንነት ካሜራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ኢንስቲትዩት የደኅንነት ካሜራዎችን ለአሚኮ አበረከተ።
Next article“የቡግና ዕውነት ከነዋሪዎቹ አንደበት”