የመድኃኒት መላመድ ፈተና!

32

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባክቴሪያዎች ራሳቸውን ለማቆየት መድኃኒቶችን የሚቋቋሙበት ወይንም የሚላመዱበት ተፈጥሯዊ ሂደት አላቸው። ይህም ጅናቸውን በመቀያየር በመድኃኒት እንዳይጠቁ ማድረግ ነው። የመድኃኒት ምላሽ አለመስጠት ወይንም የጀርሞች የመድኃኒቶች መላመድ ከዓለማችን የጤና ሥጋቶች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀስ እና የኅብረተሰብ ጤና ችግር እየኾነ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ደግሞ በተለይም ቲቢ፣ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ፣ ወባ እና ሌሎች የጤና ችግሮችን ለማከም እና ለመከላከል በሚውሉ የጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች ላይ እየተከሰተ ያለው የጀርሞች መላመድ ችግር ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። የዓለም ጤና ድርጅት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 የመድኃኒት መላመድ ዓለም አቀፋዊ አሳሳቢነት አስመልክቶ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ደግሞ ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቀጥታ በመድኃኒት ብግርነት ምክንያት በየዓመቱ ይሞታሉ።

ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በተዘዋዋሪ መልኩ በመድኃኒት መላመድ ምክንያት ሕይዎታቸው ያልፋል። ድርጅቱ አፍሪካ ላይ ባደረገው ጥናት ደግሞ በዓመት 1 ሚሊዮን ሰዎች ሕይዎታቸውን ያጣሉ። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የመድኃኒት መላመድ መድኃኒቶችን በትክክል አለማዘዝ፣ ማኅበረሰቡ ደግሞ የታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ እና በሰዓቱ አለመውሰድ እና የታዘዙ መድኃኒቶችን መጠን በመቀነስ ሊከሰት ይችላል።

መድኃኒት የተላመዱ በሽታዎችን ለመከላከል በመንግሥት በኩል የመመርመሪያ እና የማከሚያ አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን በማስገባት እየሠራ ይገኛል። በተያዘው ዓመት በክልሉ የኤች አይቪ መመርመሪያ መሳሪያዎችን በክልሉ ለማስጀመር እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል። የቲቢ በሽታን ለመመርመር የሚያስችሉ 134 የሚኾኑ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ፊቸር የተጫነላቸው ማሽኖችን ለማስገባት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

ማሽኖቹ መድኃኒት የተላመዱ ቲቢዎችን በቀላሉ ይለያሉ፤ በቀላሉ ደግሞ የሚገባቸውን መድኃኒቶች የሚሰጡ ናቸው። አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን ከማስገባት ባለፈ የቲቢ ታማሚዎችን ፈልጎ ማከም ዋነኛ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለ4 ሺህ 916 የቲቢ ታማሚዎች ሕክምና እየተሰጠ ይገኛል።

ይሁን እንጅ በሽታው የሚተላለፈው በአየር ወይንም በትንፋሽ በመኾኑ የሥርጭት መጠኑ መጨመር እና መድኃኒት እየተለማመደ በመምጣቱ አስቸጋሪ አድርጎታል። በሩብ ዓመቱ ብቻ እንኳ 24 የሚኾኑ መድኃኒት የተላመደ የቲቢ ታካሚዎች መገኘታቸውን ለአብነት አንስተዋል። የመመርመሪያ መሳሪያዎችን አቅም ለማበልጸግ እና ለማዘመን እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ ማኅበረሰቡ በሕክምና ባለሙያዎች የታዘዙ መድኃኒቶችን በአግባቡ በመውሰድ በሽታውን መከላከል እንደሚገባውም አሳስበዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የመድኃኒት መላመድ ለመከላከል ዓለም ዓቀፋዊ ዕቅድ አውጥቶ እየሠራ ይገኛል። በኢትዮጵያም በፈረንጆች አቆጣጠር እስከ 2030 የሚተገበር የአንድ ጤና ማዕከል ስትራቴጅክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሠራም ነው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት እርምት እንዲወስዱ የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ አሣሠበ፡፡
Next articleየዘመቻ ሥራ የወባ በሽታ ስርጭትን ቀንሷል።