
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በልጆች የስማርት ስልክ አጠቃቀም ዙሪያ ወላጆችን ከሚፈትናቸው ነገር አንዱ በየትኛው ዕድሜ ላይ ልጆች ስልክ እንዲጠቀሙ መፍቀድ እንዳለባቸው ነው። ይህን ችግር በየትኛውም ዓለም ያሉ ወላጆች ይጋሩታል። የልጆች ስማርት ስልክ መያዝ ችግር ሊኾን የቻለባቸው በርከታ ምክንያቶች አሉ። ልጆች ከስልኮች መልካም ነገር ሊያገኙ እንደሚችሉት ሁሉ ለብዙ አካላዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ አዕምሯዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ሊጋለጡ ይችላሉ።
በሪሰርች ዶት ኮም (https://research.com/…/what-age-should-a-child-get-a… ) አይመድ ቦችሪካ የተባለ የዳታ ሳይንቲስት በቅርቡ ባወጣው ጽሑፍ የልጆች የስማርት ስልክ አጠቃቀም ያለውን ችግር ጠቅሷል። ብዙ ሰዓታትን በስልክ ላይ ልጆች የሚያሳልፉ ከኾነ በአዕምሮ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ገልጿል።
በተጨማሪም ልጆችን ከማኅበራዊ እና ቤተሰባዊ ግንኙነት በመነጠል ሊማሩት የሚገባቸውን ክህሎት እንዳያገኙ ይገድባቸዋል። ያልተገቡ ይዘቶችን እንዲመለከቱም ያደርጋል። ሌላው እና አደገኛው ነገር ደግሞ የመፍራት፣ የድባቴ እና ራስን የማጥፋት ሥነ ልቦና እንዲያዳብሩ ያደርጋል። በልጆች ላይ ሊበረታ ቢችልም በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ባሉ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ላይ የሚከሰት ሌላ ሥነ ልቦናዊ ችግርም አለ። ይህ ችግር “ኖሞፎቢያ” ይባላል። “ኖሞፎቢያ” ያለ ስልክ ለመንቀሳቀስ መፍራት እና መጨነቅ ነው።
በአሜሪካ በልጆች የስማርት ስልክ አጠቃቀም ዙሪያ የተሠራን ጥናት ዋቢ አድርጎ ቦችሪካ ሲጽፍ 53 በመቶ የሚኾኑ ሕፃናት በ11 ዓመታቸው ስልክ መጠቀም እንደሚጀምሩ ይነግረናል። በሌላ በኩል በዩናይትድ ኪንግደም 44 በመቶ የሚኾኑ ወላጆች ለልጆች ቀድሞ ሥልክ መስጠት ለትምህርታቸው ጠቃሚ መኾኑን ያምናሉ።
በየትኛውም መንገድ ግን ልጆች ስልክ እንዲጠቀሙ ለመፍቀድ የሚበጃቸውን እና የማይጠቅማቸውን ነገር መለየት በሚችሉበት ዕድሜ ላይ ሊኾኑ እንደሚገባ በድረ ገጹ ተጠቁሟል። ቴክኖሎጂ ሁለት ስለት እንዳለው ሰይፍ ነው። ለመልካም ተብሎ የተሠራው ሌላ አሉታዊ ነገሮችም ይኖሩታል። ስማርት ስልኮች ያላቸውን ጠቀሜታ ያክል ልጆች ያለ ዕድሜያቸው ሲጠቀሟቸው የሚያስከትሏቸው ችግሮች በሕይዎታቸው የሚዘልቁ ሊኾኑ ይችላሉ።
ለእነዚህ የቴክኖሎጂ ችግሮች ደግሞ ሌላኛው ቴክኖሎጂ መፍትሔ ያመጣል። የልጆችን የስልክ አጠቃቀም በተመለከተ ወላጆች የልጆችን ይዘት እና የስክሪን ቆይታ የሚከታተሉበት የልጆች ገጽ (Kids Mode) የተሰኘ መተግበሪያ ለዚህ ተጠቃሽ ነው።
የልጆች ገጽ በዘመናዊ ስልኮች አብሮ ተካቶ እየመጣ ቢኾንም ከመተግበሪያ ቋቶች አውርዶ መጠቀምም ይቻላል።
ይህን መተግበሪያ በመጠቀም የልጆችን ሁለንተናዊ ደኅንነት መጠበቅም ይቻላል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!