
ሰቆጣ: ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት “ከቅሸነ” ቲያትር እና ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር “ልጆችን በትምህርት እናሳድግ” በሚል መሪ መልዕክት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሰቆጣ ከተማ በተለያዩ ኩነቶች አክብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ሕጻናትን በመወከል የሕጻናት ፓርላማ ምክትል ሠብሣቢ ተማሪ ዓለም አወቀ ከሰሜኑ ጦርነት ወዲህ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያሉ ሕጻናት ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ገልጻለች።
እየተስፋፋ የመጣውን ያለ ዕድሜ ጋብቻ፣ የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና የሴት ልጅ ጥቃት እንዲቆም የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርባለች።
ሕጻናትን ያለ ዕድሜ መዳር ነገአቸው እንዲበላሽ መወሰን ነው ያለችው ተማሪዋ ወላጆች ከዛሬው ደስታ ይልቅ የነገውን ሰቆቃ በመገንዘብ ሕጻናትን ወደ ትምህርት እንጂ ወደ ትዳር ሊያስገቡ እንደማይገባ አስገንዝባለች።
በከተማ እየተስፋፋ የመጣው ሱሰኝነት ለሴት ልጅ ጥቃት እንደምክንያት ነው ያሉት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጌትነት እሸቱ ናቸው።
ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት ባለፉት ሁለት ዓመታት በከተማዋ የሠራው የንቅናቄ መድረክ ለውጥ እያመጣ ነው ብለዋል ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው።
የሴት ልጅን ጥቃት፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን እና የሕጻናት ጉልበት ብዝበዛን ማስቆም ለመንግሥት ብቻ የሚተው ተግባር ባለመኾኑ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
ዓለም አቀፉ የሕጻናት አድን ድርጅት በዓለምም ኾነ በኢትዮጵያ ሕጻናት ላይ የሚደርሱ የጉልበት ብዝበዛዎችን፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻን እና መሰል ጭቆናን ሊከላከል የመጣ ግብረሰናይ ድርጅት መኾኑን በሰቆጣ ቅርንጫፍ የድርጅቱ ሥራ አሥኪያጅ ምህረት ሞላ ገልጸዋል።
በቀጣይም መሰል መርሐ ግብሮችን በማካሄድ የግንዛቤ ማስጨበጡን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የነገሩን።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጋብቻ 112 ሕጻናት፣ በሱስ 413፣ በወቅታዊ የሰላም እጦት እና በድርቁ ሳቢያ ከ59ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ማቋረጣቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ ገልጸዋል።
ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ችግር ለመከላከል አሥተዳደር ምክር ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መኖሩ ሕጻናት ሃሳባቸውን እንዲያቀርቡ አጋዥ ድርጅቶችም በነጻነት እንዲያግዙ የሚያስችል በመኾኑ ያለውን ሰላም መጠበቅ ይገባል ነው ያሉት።
በመርሐ ግብሩም የጎዳና ላይ ሩጫ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ አስተማሪ ድራማዎች እና መልዕክቶች ተላልፈዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች፣ የየወረዳ ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ መምህራን እና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!