
ባሕር ዳር: ኅዳር 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር የ2020 የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዘ በየቀኑ የ800 ሴቶች ሕይዎት ያልፋል። ከዚህ ውስጥ 95 በመቶ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ የሚከሰት ነው።
ድርጅቱ ይፋ እንዳደረገው በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ዓመት 14 ሚሊዮን እናቶች በወሊድ ወቅት ከፍተኛ የኾነ ደም መፍሰስ ያጋጥማቸዋል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 70 ሺህ የሚኾኑት ሕይዎታቸውን ያጣሉ።
በአጠቃላይ በዓለም ሕይዎታቸው ካለፈው እናቶች ውስጥ 75 በመቶ የሚኾኑት ከፍተኛ የደም መፍሰስ በተለይም ደግሞ ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥም ደም መፍሰስ፣ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም የደም ግፊት፣ “ኢንፌክሽን”፣ ውስብስብ የኾነ ወሊድ እና ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ ዋና ምክንያቶች ኾነው ተቀምጠዋል።
በኢትዮጵያ 14 ሺህ የሚኾኑ እናቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ሕይዎታቸውን እንደሚያጡ መረጃዎች ያሳያሉ። የእናቶች በጤና ተቋማት ክትትል ምን እንደሚመስል ከአንዲት ነፍሰጡር ጋር ቆይታ አድርገናል። ወይዘሮ ሕይዎት በላይ ትባላለች፤ ነፍሰጡር ስትኾን የመጀመሪያዋ እንደኾነ ገልጻ የመጀመሪያ ልጇን ለመሳም ሁለት ወራት እንደሚቀሯት ትገልጻለች።
ላለፉት ሰባት ወራትም በሰሜን ወሎ ሸድሆ መቄት ሆስፒታል በየወሩ ክትትል እያደረገች ትገኛለች። ሕይዎት እንዳለችው የጤና ባለሙያዎች እናቶች ማድረግ ስለሚገባቸው ነገሮች በየጊዜው ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ፤ አጠቃላይ የጤና ክትትልም ያደርጋሉ። ክትትሉ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በመለየት ሕክምና ለመስጠት እንዲቻል የታሰበ ነው።
ቀድሞ ክትትል ማድረግ በመቻሏ የመጀመሪያዎቹ ሦስት የእርግዝና ወራት አጋጥሟት የነበረው ሕመም መቀረፉን ነግራናለች። በመደበኛነት ከሚደረገው ክትትል ባለፈ የተለየ ስሜት ከተከሰተ ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ትምህርት እንደሚሰጡ ትገልጻለች።
በጤና ተቋማት ክትትል በማድረጓ መጀመሪያ ከነበረው የፍርሃት እና ጭንቀት ስሜት በመላቀቅ የሥነ ልቦና ዝግጅት ለማድረግ እንዳገዛትም ነግራናለች። በአማራ ክልል ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችለውን ሞት ለመቀነስ ሢሠራ ቢቆይም በሰሜኑ ጦርነት ክትትሉ መዳከሙን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች ሕጻናት እና ወጣቶች ዳይሬክተር መልሰው ጫንያለው ገልጸዋል።
ጦርነቱ መጠናቀቁን ተከትሎ እናቶች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ነፍሰጡሮችን ቀድሞ በመለየት፣ ግንዛቤ መፍጠር እና የክትትል ሥራ ሢሠራ ቆይቷል ብለዋል። ለትራንስፖርት ምቹ ባልኾነባቸው እና ከጤና ተቋማት ርቀት ባላቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነፍሰ ጡሮችን ደግሞ በእናቶች ማቆያ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
ይሁን እንጅ በ2016 ዓ.ም 75 በመቶ የሚኾኑ ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ታቅዶ ወደ ሥራ ቢገባም በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተደራሽ ማድረግ የተቻለው 59 በመቶ ብቻ ነው። በ2017 ዓ.ም 82 በመቶ ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዚህም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በጤና ተቋማት መውለድ ከሚገባቸው ውስጥ አገልግሎቱን ያገኙት 55 በመቶ ብቻ ናቸው። የዓለም ጤና ድርጅት አንድ እናት እስከ ስምንት ጊዜ በጤና ተቋማት ክትትል ማድረግ እንዳለባት ቢያስቀምጥም በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአንዲት እናት የአራት ጊዜ ክትትል ምጣኔ እንኳ ከ64 በመቶ ማለፍ አለመቻሉን ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
በጤና ተቋማት እየተገለገሉ የሚገኙትም የተሻለ ግንዛቤ እና የትምህርት ደረጃ ያላቸው ናቸው። የጤና መዋቅሩ ግንኙነት መቆራረጥ፣ የሚቀርበው ግብዓት ውስን መኾን፣ ግብዓቱ ወደ ክልሉ ከደረሰ በኋላም በጸጥታው ችግር ምክንያት በወቅቱ በሁሉም ጤና ተቋማት አለማድረስ መሠረታዊ ችግር ኾነው ተቀምጠዋል።
ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ አንቡላንሶች መበላሸት እና የሚሠሩትም በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት አለመቻል ሌላው ችግር ነው። ችግሩን ለመፍታት በሌሎች የተሽከርካሪ አማራጮች ጭምር ወደ ጤና ተቋማት እንዲደርሱ እየተደረገ ነው። አሁንም ያሉትን አንቡላንሶች በሙሉ አቅም ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ እና ግብዓት ወደ ተቋማት በወቅቱ እንዲደርስ ሁሉም እንዲተባበር ጠይቀዋል።
የመንግሥት ተቋማት ተሽከርካሪዎችም አገልግሎት እንዲሰጡ እና ማኅበረሰቡ ትራንስፖርት እስካለበት ድረስ እንዲያግዝም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!