
ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓለማችን ቁጥር አንድ ሃብታም ኤለን መስክ ንብረት የኾነው ነውራል ሊንክ ኩባንያ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማገዝ ጭንቅላት ላይ በቀዶ ጥገና የሚገጠም መሳሪያ በሙከራ ደረጃ በካናዳ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃድ ማግኘቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ሙከራዎችም ተጀምረዋል።
ካናዳዊው የጭንቅላት ቀዶ ጥገና ሐኪም አንድሬስ ሎዛኖ ከኤለን መስክ ጋር በመተባበር የኒውራል ሊንክ የምርምር ሥራን የአካል ክፍሎቻቸው አልታዘዝላቸው ባላቸው በሽተኞች ላይ ለመሞከር ፈቃድ አግኝተዋል ። የካናዳ የጤና ባለሥልጣናት ናቸው ሙከራ እንዲደረግ ፈቃድ የሰጡት። የምርምር ሥራው ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ ለሙከራው ፈቃደኛ የኾኑ በሽተኞችም በመመልመል ላይ ናቸው።
የሳንቲም መጠን ያለው መሳሪያ ሲኾን የቀዶ ጥገና ሥራው በሮቦት የታገዘም ይኾናል። ኒውራል ሊንክ አዕምሮ ከኤሌክትሮኒክ መሳሪያ ጋር እንዲናበብ በማድረግ ሰዎች በሃሳባቸው ብቻ ሌሎችን ቁሶች መቆጣጠር የሚችሉበትን ቴክኖሎጂ የፈጠረው ድርጅት ሥም ነው፡፡ የዚህ ድርጅት ባለቤትም ታዋቂው ባለሀብት ኤለን መስክ ነው፡፡
ከአዕምሮ ጋር እንዲናበብ ኾኖ የተሠራው ይህ መሳሪያ ዘ ሊንክ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲኾን የአካል አለመታዘዝ (ፖራሊስስ) ያለባቸውን ሰዎች ለመርዳት ሲባል በቀዶ ጥገና በጭንቅላት ውስጥ የሚገጠም ነው፡፡ የአዕምሮን ተግባራት በመመዝገብ እና በመተንተን ጉዳት ያለባቸው ሰዎች በሃሳባቸው ብቻ ቁሶችን መቆጣጠር እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡
ሴረብረም በመባል የሚጠራውን የአንጎል ክፍል የሚሸፍነው የውጨኛው ክፍል (ሴሬብራል ኮርቴክስ) ላይ ያለን ማንኛውንም እንቅስቃሴ ከመዘገበ በኋላ የነርቭ መልዕክቶችን መልሶ ለአንጎል በመላክ መሳሪያው እና አዕምሮ በሚያደርጉት መናበብ ነው የሚሠራው።
በዚህ መሳሪያ በመደገፍ የሚሰጠው ሕክምና ዓላማ አድርጎ የተነሳው በፊት የነበረው የሕክምና አቅም የአካል ጉዳታቸውን ያላስተካከለላቸውን ሰዎች ለመርዳት፣ የሰውነታቸው ክፍል አዕምሮ ላይ በደረሰ ጉዳት አልታዘዝላቸው ያላቸውን ለመደገፍ፣ የትውስታ እና የመረዳት አቅምን ለማጎልበት፣ የነርቭ ህዋስ መዛባት ችግር ያለባቸውን ለማከም እና ለመሰል ተግባራት አገልግሎት ላይ የሚውል ነው፡፡
በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ በአንድ ግለሰብ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሞከሩን እና ውጤት መታየቱን ኤለን መስክ ተናግሮ እንደነበር አልጄዚራ ባሳለፍነው ጥቅምት 22 ቀን ባወጣው ዘገባ መግለጹ ይታወሳል፡፡ መጀመሪያ ተሞክሮ የነበረው መሳሪያ ቴሌፓዚ የሚባል ሲኾን ሰዎች በማሰብ ብቻ ስልካቸውን ወይም ኮምፒውተራቸውን መቆጣጠር የሚችሉበት መኾኑንም መስክ ገልጾ ነበር፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!