
ደብረ ብርሃን: ኅዳር 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሚዲያ ባለሙያዎች ለሥነ ተዋልዶ ጤና በትኩረት እንዲሠሩ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን በሥነ ተዋልዶ ጤና የጋዜጠኝነት ዘውግ የሠራችው ጋዜጠኛ ሶሶና ተስፋዬ ተናግራለች።
በዚህ ዘርፍ የሚሰማሩ ጋዜጠኞችን ማፍራት ከተቻለ ጥልቅ የኾነ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤ እና ዕውቀት እንዲኖራቸው የሚያግዝ በመኾኑ ለአድማጭ፣ ተመልካች እና አንባቢያን ጥራት ያለው መረጃ ለማድረስ ያስችላል ብላለች።
ሥነ ተዋልዶ ጤናን በተመለከተ መገናኛ ብዙኅን የሚሠሯቸው ዘገባዎች የቃላት አጠቃቀም ችግሮች የሚስተዋልባቸው መኾኑንም አስረድታለች። ለአብነትም ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ለማለት ተፈልጎ በስህተት ቫይረሱ ያለባቸው ወገኖች ሲባል እንደሚስተዋል ነው የገለጸችው። የዕድሜ ማራዘሚያ ከምንል የጸረ ኤች አይቪ መድኃኒት ቢባል ተመራጭ እንደኾነ እና ሴተኛ አዳሪ ማለት ሲገባ በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች፤ ያልተፈለገ እርግዝና ከሚባል ይልቅ ጽንስ ማቋረጥ ቢባል ተመራጭ ነው ብላለች።
መገናኛ ብዙኅን መረጃ ሲያደርሱ ኅብረተሰቡ በጨዋ ደንብ የሚገልጻቸውን ቃላት በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ መኾኑን ገልጻለች። መገናኛ ብዙኀን ለዜና የሚሰጡት ትኩረት የላቀ እንደኾነ ሁሉ የሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ፈጠራ የታከለባቸው ሥራዎችን በአንክሮ በመሥራት ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል ስትል ጋዜጠኛ ሶስና ሃሳቧን አጋርታለች ።
ዘጋቢ፦ ሀብታሙ ዳኛቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!