
ባሕር ዳር: ኅዳር 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሃሳብ ወደ ኋላ ብዙ ዓመታትን ተጉዘን ብንሄድ የሰው ልጅ የፍላጎቱ ውጤት የኾኑ በርካታ ፈጠራዎችን እና ያለፉበትን የለውጥ ሂደት እንድናስብ ያግዘናል። በፈጠራ ሥራቸው ሕይዎትን ያቀለሉ በርካታ ሰዎች አበርክቷቸው ያለውን ጠቀሜታ እንድናስብ እና ምሥጋናን እንድንቸራቸው ያግዘናል።
በዘመን ጅረት ውስጥ በሚገርም ፍጥነት የለውጥ ሂደት ላይ የነበረው እና አሁንም እያደገ ያለው ዘርፍ የመረጃ እና ተግባቦት ቴክኖሎጂ ነው። እጅግ ብዙ የፈጠራ ባለሙያዎችን አያይዘን ልንጠቅሰ እንችላለን። ነገር ግን የፈጠራ ሥራን ከሌላ ጎልቶ የወጣ ሙያ ጋር አቆራኝቶ የያዘ ሰው ግን ብዙም የተለመደ አይደለም።
እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በኦስትሪያ ቬና የተወለደች ድንቅ ተሰጥኦ እና አበርክቶ የነበራት ውብ ሴት ፈለቀች፤ ሄዲ ለማር ትባላለች። አሁን ለደረስንበት የመረጃ ዘመን እጅግ ወሳኝ የኾነ የፈጠራ አስተዋጽኦ የነበራት ናት። ላማር የውበት ተምሳሌት ተደርጋ የምትወሰድ፣ መልከ መልካም፣ አዲስ ነገር ማወቅ የምትፈልግ እና ብሩህ አዕምሮ ያላት ነበረች።
ገና ከ16 ዓመቷ ጀምራ በትወናው ዘርፍ ጎልታ መውጣት የቻለች ናት። ከቬና ወደ ፓሪስ ከዛም ወደ ለንደን በመጓዝ የትወና ብቃቷን አሳድጋለች። ለንደን ውስጥ ሉዊስ ሜየር ከሚባል የትወና ባለሙያ ጋር የመተዋወቅ ዕድል አግኝታ በሆሊውድ ፊልም መሥራት የሚያስችላት የውል ስምምነት አመቻችቶላት ወደ አሜሪካ ተጉዛ ከ30 በላይ ፊልሞች ላይ ተውናለች።
በ1940ዎቹ መግቢያ ላይ የሠራቻቸው ቡም ታውን እና ዋይት ካርጎ በተሰኙ የፊልም ሥራዎች ትልቅ ዕውቅናን አበርክቶላታል። ከሁሉም በላይ ተወዳጅነትን እና ዝናን ያተረፈላት ግን የሶምሶን እና የደሊላን ታሪክ የሚያትተው መንፈሳዊ ይዘት ያለው ፊልም ነበር። በ1960 በሆሊውድ የዝና ታሪክ ቁንጮ ላይ የነበረች ሴትም ናት።
ይህቺ ሴት ታዲያ በውበቷ አሊያም በትወና ብቻ አይደለም አድናቆትን እና ዝናን ያካበተችው። በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዘርፍም ጉልህ ሚናን ተጫውታለች። በፈጠራው ዘርፍ የሚያግዛት መደበኛ ትምህርት አሊያም ሥልጠና አልወሰደችም ነገር ግን ትርፍ ጊዜዋን በቴክኖሎጂ ዲዛይን እና በፈጠራ ንድፈ ሃሳብ ላይ ምርምር በማድረግ ታሳልፍ ነበር።
የትራፊክ መብራት ላይ የማሻሻያ ሥራ ሠርታለች በዋናነት ደግሞ አሁን ላለንበት የገመድ አልባ የመረጃ ግንኙነት ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው ፍሪኩዌንሲ ሆፒንግ የተባለ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤት ናት። ይህ የምርምር ሂሳብ ወደ አዕምሮዋ የገባው በ1930ዎቹ አካባቢ ከባሕር ኀይል ባለቤቷ ፍሪትዝ ማንድል ጋር አብራ ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ በሚመክር ሥብሠባ የመሳተፍ ዕድል ባገኘችበት አጋጣሚ ነበር።
ከሥብሠባው የባሕር ኀይሉ ለወታደራዊ አገልግሎት የሚጠቀማቸው ተተኳሾችን መቆጣጠር የሚችልበት ሥርዓት እንደሚያስፈልገው ተረዳች። ተተኳሾችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የሬዲዮ ሞገድ ሥርዓት ቀደም ሲል አገልግሎት ላይ ይውል የነበረ ቢኾንም በጠላት መጠለፍ ወይም መደናቀፍ የሚችል ነበር።
ይህን ችግር ፈች ብላ ያደራጀችው ሃሳብ ፍሪኩዌንሲ ሆፒንግ ሲኾን በወታደራዊ ዘርፍ ተተኳሾች በጠላት ጣልቃ ገብ የሬዲዮ ሞገድ (ጃም) እንዳይደናቀፉ የሚያደርግ ነው።
ፍሪኩዌንሲ ሆፒንግ ማለት የሬዲዮ መልዕክቶችን በፍጥነት በሚቀያየር ፍሪኩዌንሲ በማስተላለፍ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ሳይበግረን እና የሞገድ መጠለፍ (ጃም) ሳያጋጥም መቆጣጠር የምንችልበት ነው።
የጀ.ፒ.ኤስ፣ ብሉቱዝ እና ዋይፋይ ቴክኖሎጂዎች አሁን ለደረሱበት ደረጃ መሠረት ተደርጎ የሚታይ ፈጠራም ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!