ለዓለም የፋይናንስ ሥርዓት አማራጭ ያመጣው ሳቶሺ ናካማቶ ማን ነው?

48

ባሕር ዳር: ኅዳር 5/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የዓለምን ሥርዓት በእጅጉ እየቀየረ ያለ ነገር ነው። በጉልህ እያሳደገው ካለው ዘርፍ ውስጥ አንዱ ፋይናንስ ነው። ግብይትን፣ የገንዘብ ልውውጥን እና የባንክ ተግባራትን ቀላል፣ ቀልጣፋ እና ተመራጭ አድርጓል። በእጅ ስልክ የትም መሄድ ሳይጠበቅብን ገንዘብ መቀበል እና መላክ እንችላለን። ይህ ሁሉ ግን በማዕከላዊ የባንክ ሥርዓት ውስጥ የሚከናውን ነው።

ከዚህ ማዕከላዊ ከኾነው የባንክ ሥርዓት ያፈነገጠ አሠራር ከ15 ዓመት በፊት ሳቶሺ ናካማቶ በሚባል ግለሰብ ወይም ቡድን ተፈጥሯል። ይህ ፈጠራ ቢትኮይን ነው። ቃሉ በጣም የተለመደ ነገር ግን ብዙ እንቆቅልሾችን በውስጡ የያዘ ነው። ከእንቆቅልሾቹ መካከል የዚህ ቴክኖሎጂ ፈጣሪ ለምን ራሱን ደበቀ እና ማን ነው የሚሉ ጥያቄዎች የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነው።

የዓለምን የፋይናንስ ሂደት መቀየር የቻለውን ይህን አስገራሚ ቴክኖሎጂ የፈጠረው ግለሰብ ወይም ቡድን ዝና እና ሃብት በሚወደድበት ዓለም እየኖረ ለምን ራሱን መደበቅ ፈለገ? ትልቅ እና መልስ ያልተገኘበት ጥያቄ ነው። ሳቶሺ ናካማቶን ሊኾኑ ይችላሉ ተብለው የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች አሉ ። ከእነዚህ ውስጥ ሌን ሳሳማን ፣ ኒክ ስዛቦ፣ አዳም ባክ ፣ ሃል ፊኔ እና ፒተር ቶድ ተጠቃሾች ናቸው።

በርከታ መላምቶች ቢሰጡም ከእነዚህ ውስጥ የዕውነት ሳቶሺ ናካማቶ አለ ወይ ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚኾን ነገር አልተገኘም። ድብቁ ሳቶሺ ናካማቶ የፈጠረው ቢትኮይን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 ተፈጥሮ ለነበረው የፋይናንስ ቀውስ ምላሽ ተበሎ የተፈጠረ ትልቅ ዋጋ ያለው ዲጂታል ገንዘብ ነው። ይህ መረጃ በተጠናቀረበት ሰዓት የነበረው 1 የቢትኮይን ዋጋ በብር ሲመነዘር ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።

በቅርቡ ኤች.ቢ.ኦ የተባለው የቴሌቪዥን መረብ በለቀቀው ዘጋቢ ፊልም ከተጠርጣሪዎች ውስጥ ፒተር ቶድ የተባለውን ግለሰብ ሳቶሺ ናካማቶ ነው ብሎ ነበር ። ይሁን እንጂ ይህ ሰው ስህተት ናችሁ በሚል ውድቅ አድርጎታል።

በአንድ ወቅት ዶሪያን ናካማቶ የተባለ ግለሰብም ተመሳሳይ ነገር ገጥሞት ነበር። ሰውየው ያለውን የመረጃ ደኅንነት እና ቴክኒካዊ ዕውቀት ግምት ውስጥ በማስገባት ሳቶሺ ናካማቶ አንተ ነህ የሚል ውዝግብ ተፈጥሮበት ነበር ። ቢኾንም ሰውየው ሊቀበለው አልቻለም።

ኩለን ሆባክ የተባለው የፊልም ባለሙያ ያስተዋወቀው “ማኒ ኤሌክትሪክ ዘ በትኮይን ሚስትሪ” በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም የዚህን ምሥጢራዊ ሰው ማንነት የሚጠቁም ፍንጭ ሰጥቷል። ቢኾንም አሁንም ድረስ በእርግጠኝነት እገሌ ነው ብሎ በድፍረት ማወቅ አልተቻለም።

ሳቶሺ ናካማት ቢትኮይንን ከማስተዋወቁ ከአንድ ዓመት በፊት “ቢትኮይን:- ኤ ፒር ቱ ፒር ኤሌክትሮኒክ ካሽ ሲስተም” የሚል አርዕስት ያለው የጽሑፍ ሰነድ ይፋ አድርጎ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ቢትኮይንን ሲገልጽ ምንም ዓይነት ማዕከላዊ ጣልቃ ገብነት የሌለበት የላኪ እና ተቀባይ ግንኙነት ያለው ሥርዓት ብሎታል።

ይህ ዲጂታል ገንዘብ የተፈጠረበት ዓላማ ያልተማከለ የገንዘብ ልውውጥ የሚደረግበትን የዲጅታል ፋይናንስ ሥርዓት መፍጠር ነው።

ቢት ኮይንን ለመጠቀም በስልክ አለያም በኮምፒውተር ዲጂታል ዋሌት (የገንዘብ ቦርሳ) መተግበሪያ መጫን ያስፈልጋል።

መተግበሪያው የዋሌት አድራሻ ይሰጠናል። አድራሻውን በመጠቀም ግብይት መፍጠር ይቻላል።

በግብይት ሂደት ደግሞ የሚኖርን መረጃ ባልተማከለ መንገድ የሚመዘግብልን ብሎክቼይን የተባለ ዲጂታል ሰነድ አለ። በመኾኑም ማዕከላዊ የቁጥጥር የሌለው ያልተማከለ የፋይናንስ ሥርዓት ይፈጥራል ማለት ነው።

ይህን ለዓለም የፋይናንስ ሥርዓት አማራጭ ያመጣ አካልን ማወቅ የቻለ የለም እኔ ነኝ ብሎ ማረጋገጥ የቻለም የለም።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍና ሌሎች አቅርቦቶች ተደራሽ እንዲኾኑ የተግባቦት ሥራው እንዲጠናከር የሚጠይቅ መድረክ ተካሄደ።
Next articleየአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች ዕውቅና እና ሽልማት አበረከተ፡፡