የ5ኛ ትውልድ የመረጃ መረብ!

67

ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመረጃ መለዋወጫ አማራጮች ከሰው ልጅ ዕድገት ጋር አብረው እያደጉ፣ እየተለወጡ እና ፍላጎትን እየሞሉ ዘመናትን ተሻግረዋል። ባሕላዊ በኾነ መንገድ መረጃን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመላክ ብዙ አይነት ስልቶች በተለያዩ አካባቢዎች ይተገበሩ ነበር። እነዚህ መንገዶች በጽሑፍ፣ በምልክቶች እና በድምጽ ጭምር ይከናወኑ ነበር።

የመገናኛ ዘዴ እያደገ መምጣት ዘመናዊ አማራጮች እንዲፈጠሩ አድርጓል። እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1979 መረጃን በድምጽ ብቻ ማስተላለፍ የሚቻልበት የአንደኛው ትውልድ የመረጃ መረብ ሲፈጠር እንደ ትልቅ ዝማኔ ይቆጠር ነበር። ነገር ግን የጽሑፍም ኾነ የምስል መረጃን የሚያስተላልፍ አልነበረም። በድምጽ ብቻ ነበር የሚሠራው።

በዘመን መንጎድ እና በሰው ልጅ የማይሞት የለውጥ ፍላጎት በሂደት አሁን ላይ ደርሰናል። የመረጃ መለዋወጫ አማራጮች 5ኛ ትውልድ የመረጃ መረብ ላይ ደርሷል። የ5ኛ ትውልድ የመረጃ መረብ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 አካባቢ ነው ለዓለም የተዋወቀው። ኢትዮጵያ ለመድረስ ደሞ አምስት ዓመታትን ፈጅቶበት አሁን ላይ በተለያዩ ከተሞች አገልግሎቱ ጀምሯል።

5ጂ ከሁሉም የኔትወርክ ትውልዶች የላቀ አቅም ያለው እና በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ቴክኖሎጂ ነው። ቴክኖሎጂው ከእሱ በፊት ከነበረው የ4ጂ ኔትወርክ በ100 እጥፍ የሚልቅ ፍጥነት አለው። ይህ ፍጥነቱ በነበረው ኔትወርክ ማከናወን ያልተቻሉ ተግባራትን ለማከናወን ወሳኝም ነው።

ለምሳሌ ትልቅ መጠን ያላቸውን ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለማውረድ እና ለመጫን፣ ለሰው አልባ ተሽከርካሪዎች የተግባቦት ሥራ፣ ለረቀቁ ፋብሪካዎች (smart factories)፣ ለረቀቁ ከተማዎች (Smart cities)፣ ለረቂቁ የጤና አገልግሎቶች (smart health care) እና መሰል ዘርፎች ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።

በጣም ፈጣን ነው ሲባል በአንድ ሴኮንድ ውስጥ እስከ 10 ጊጋባይት መጠን ያለውን መረጃ መላክም ኾነ ማውረድ ያስችላል። በረቀቁ ፋብሪካዎች ውስጥ ፈጣን የዲጅታል መረጃ ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ የተቀላጠፈ ምርት እና ምርታማነት ይፈጥራል። ረቂቅ (smart) አገልግሎቶችን ሲያሳልጥ በርካታ ሥራ እና የሥራ ዕድልም ይፈጥራል። የቢዝነስዋየር ድረገጽ መረጃ 5ጂ እስከ 2034 አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ከ5ጂ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ይፈጥራል ተብሎ ከተተነበየለት ውስጥ 100 ሺህ የሚኾነው ሥራ አሁን ላይ መፈጠሩን ይነግረናል።

ይህ ቴክኖሎጂ ከሌሎች ትውልዶች በፍጥነቱ እና በጥራቱ የተሻለ መኾኑ ከሌሎቹ እንዲልቅ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሚጠቀማቸው ትራንስሚተሮች ትንሽ መጠን ያላቸው በመኾናቸው የሚጠቀመው ኀይል ትንሽ ነው። የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ካለው ማደግ ጋር ተያይዞ የኢንተርኔት መሳሪያዎች (IOT) ትስስር እየጨመረ የሚሄድ በመኾኑ ጠንካራ እና ጥራት ያለው ግንኙነት እንዲኖራቸው በማድረግ ያግዛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዩኒቨርስቲው የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሀገር በቀል እውቀት ላይ እየሠራ መኾኑን ገለጸ።
Next articleከ472 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ ጅቡቲ ወደብ መድረሷ ተገለጸ፡፡