
አዲስ አበባ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ)19ኛው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አህጉራዊ ሥብሠባ በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡ በሥብሠባው መክፈቻ ላይ የኢፌዴሪ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ድኤታ ያስሚን ውሀረቢ አፍሪካ ያላትን አቅም እንዴት መጠቀም እንደሚገባት የሚያሳይ ሥብሠባ ነው ብለዋል።
ዛሬ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለማፋጠን ነው የተገኘነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ የአማካሪ ሚኒስትሮች ጉባኤው በአግባቡ እንደሚመክርበት አብራርተዋል። ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጣናን ሲተገብሩ አንድነታቸውን አስጠብቀው እና የሀገራቸውን ጥቅምም ጠብቀው እንደሚኾን ተናግረዋል። የአፍሪካ የቢዝነስ -ለቢዝነስ ግንኙነት እና ድንበር ዘለል የንግድ ሥራን በአግባቡ መከወን እንደሚገባም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ለነፃ የንግድ ቀጣና ያላትን ቆራጥነት የሚያሳይ ተግባር መፈጸሟንም ነው ያስገነዘቡት። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ፆጤፂ ማኮንግ (ዶ.ር) “ኢትዮጵያ የእኛ የጋራ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ምሳሌ ኾና ታገለግለናለች፤ መነሻ የሚኾን በቂ ማሳያም አለን” ብለዋል። የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ይሳካ ሲባል ያለችግር እና እንቅፋት ሊኾን አይችልም፤ በመኾኑም ይህንን በማለፍ ለአፍሪካ የሚጠቅም ነገር መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ዝም ብሎ ንግድ አይደለም ያሉት ዋና ጸሐፊው ብልጽግና፣ ዕድል እና አንድነት ነው ብለዋል። አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የልማቱ ዋነኛ ማቀጣጠያ በማድረግ መጠቀም እንደሚገባም ተጠቁሟል። ያለውን ወጣት የሰው ኀይል በአግባቡ በመጠቀም ሥራ በመፍጠር ከሚቀያየረው የቴክኖሎጂ ለውጦች ጋር በማዋሀድ በአፍሪካ ምድር ላይ ጠቃሚ ነገር እንዲሠራም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!