“በ2017 ዓ.ም በመስኖ 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታስቦ ወደ ተግባር ተገብቷል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

67

ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክልል የተትረፈረፈ የገጸ ምድር እና ከርሰ ምድር የውኃ ሃብት ካላቸው ክልሎች ከንዱ ነው። ክልሉ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት አቅም እንዳለው ቢታመንም እስከአሁን የለማው ከ11 በመቶ እንደማይበልጥ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።

በ2016 ዓ.ም እንኳ 300 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በማልማት 40 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት መቻሉን ማንሳት ይቻላል። በ2017 ዓ.ም 342 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዷል። በልማቱ ደግሞ ከ1 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ።

ወደ ተግባር ከገቡት አርሶ አደሮች ውስጥ በምዕራብ ደምቢያ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ቁምላቸው ዳኘው ይገኙበታል። ለአርሶ አደር ቁምላቸው በመስኖ ሁለት ጊዜ ማምረት የተለመደ ሥራ ነው። በተለይ ደግሞ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከተለመደው ሰብል በመውጣት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት ስንዴን በኩታ ገጠም ማልማት ችለዋል። በሄክታርም እስከ 40 ኩንታል ማግኘት መቻላቸውን ነግረውናል።

ሌላኛው አርሶ አደር አጣናው ሙሉነህ የጣና ሐይቅን በመጠቀም ባለፈው ዓመት በውስን መሬት ላይ ሽንኩርት በማምረት ቋሚ ሃብት ማፍራት ችለዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ አንድ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ ሽንኩርት፣ አትክልት እና ስንዴ ለማምረት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። አካባቢው ጣናን ጨምሮ የውኃ ሃብት ያለበት በመኾኑ በዓመት ሁለት ጊዜ የማምረት እቅድ እንዳላቸው ገልጸውልናል።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና መስኖ ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው እንዳሉት በ2017 ዓ.ም 342 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ወደ ተግባር ተገብቷል። ከዚህ ውስጥ 230 ሺህ ሄክታር መሬት በአንደኛ ዙር የመስኖ ስንዴ የሚለማ ይኾናል። 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል።

በዚህ ዓመት ከባለፉት ዓመታት በተለየ መንገድ ቀድሞ ወደ ተግባር መገባቱንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ በመስኖ ለማልማት ከታቀደው መሬት ውስጥ 54 ሺህ 984 ሄክታሩ ታርሷል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 34 ሺህ 621 ሄክታሩ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል። ከታረሰው ውስጥ 24 ሺህ ሄክታሩ ለስንዴ የታረሰ ሲኾን 1 ሺህ 861 ሄክታሩ በስንዴ ተሸፍኗል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ለስንዴ መስኖ ከሚያስፈልገው ከ300 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ዘር እስከ 90 በመቶ የሚኾነውን አርሶ አደሮች በመኸር ካመረቱት በልውውጥ እንዲሸፍን እየተሠራ ይገኛል። 500 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ መስኖ ወደሚለማባቸው ቦታዎች የማዘዋወር ሥራ ተሠርቷል። መጋዘን ላይ የሚገኘውንም የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ከ20 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚያለሙ 5 ሺህ አዲስ የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን የማሠራጨት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። እስከ አሁንም ከ3 ሺህ በላይ የሚኾኑት ወደ አርሶ አደሮች ተሰራጭተዋል። ከ36 ሺህ በላይ ነባር የውኃ መሳቢያ ሞተሮች ደግሞ ሌላው የልማቱ አቅም ናቸው።

በተለይም ደግሞ ለስንዴ ልማት ትራክተር እና ኮምባይነር መጠቀም ሌላው አማራጭ ተደርጓል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። በዚህ ዓመት የተጠናቀቁ 5 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚችሉ መካከለኛ እና አነስተኛ የመስኖ መሠረተ ልማቶች ሌላ ግብዓቶች ናቸው። 1 ሺህ 857 ኪሎ ሜትር የቦይ ጠረጋ ሥራም እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።

በመስኖ ሥራ ከሚሳተፉት ውስጥ እስከ አሁን 584 ሺህ 175 ለሚኾኑ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሠርቷል። ቀሪውም በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል።

በክልሉ በመስኖ የሚመረተው መሬት በመኸር ከሚመረተው መሬት 5 በመቶውን፣ በመኸር ከሚመረተው ምርት ደግሞ 30 በመቶ ይሸፍናል። ይህም በትንሽ መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት ማምረት እንደሚቻል ተሞክሮና ልምድ የተቀሰመበት መኾኑን አቶ ይበልጣል ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ስንዴ በበልግ፣ በመስኖ እና በመኸር እየተመረተ ይገኛል። ባለፉት ዓመታት በስንዴ ላይ በተሠራው ሥራም ወደ ክልሉ ይገባ የነበረውን የሥንዴ ምርት ማስቀረት መቻሉን ዳሬክተሩ ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ቀድሞ የመስኖ ሥራ መጀመሩ የተሻለ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና መሪዎች እጅ እና ጓንት ኾነው ሰብልን እንዲሠበሥቡ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ።
Next article“ተቋማት እና መንግሥት በሰብዕና ግንባታ ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ ይገባል” ተድላ ኩታዬ (ዶ.ር )