
ባሕር ዳር: ጥቅምት 10/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እንደ ሮኬት ተመንጥቃ ከወጣችበት ጥንታዊ እና ቀደምት የከፍታ ታሪኳ ይልቅ እንደ ናዳ ተምዘግዝጋ የወረደችበት አሁናዊ የቁልቁለት ተረኳ በብዙው ያስቆጫል፡፡
ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ እንደ ኮኮብ አብርታ እንደ ዘበት መዘንጋቷ አስተውሎ ላሰበው ልብ ይሰብራል፡፡ “አግኝቶ ማጣት፤ ቀድሞ መመራት የእግር እሳት ነው” ይላሉ ኢትዮጵያውያን በብሂላቸው፡፡
በዓለም ላይ ከተመዘገቡት አራት ታላላቅ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች መካከል የዚች ሀገር ቀደምት ሥልጣኔ አንዱ ነበር ቢባልስ ማን በቀላሉ ሊያምን ይችላል፡፡ የባቢሎን እና የሮም ሥልጣኔዎችን ተከትሎ የጥንታዊ ቻይናን ሥልጣኔ አስከትሎ የመጣው የአክሱም ሥልጣኔ መሥራች ልጆች ነበርን ማለትስ ምን ያክል ያሳምናል?
ኸኸኸቀደምት ሥልጣኔዎቻችንን እንዳንክድ ከየሃ እስከ ሮሃ፤ ከጎንደር እስከ አፋር፣ ከዳማት እስከ ጋፋት አሻራዎቹ አሁንም ድረስ ህያው ናቸው፡፡ አምነን እንዳንቀበል ደግሞ የወረድንበት ቁልቁለት እና የተምዘገዘግንበት ፍጥነት ከአዕምሮም በላይ ነው፡፡
የዘመን አቆጣጠርን የቀመረው፣ በሥነ ፈለክ ላይ የተራቀቀው፣ ሲራራ ንግድን ያስተዋወቀው፣ ሥነ መንግሥትን ያረቀቀው፣ ኪነ ጥበብን ያስተዋወቀው፣ በሥነ መለኮት የራቀው፣ በኪነ ህንጻ የተራቀቀው የዚያ ዘመን ታላቅነት ደብዛው ለምን እንዲህ ጠፋ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
በእርግጥ ታሪክ እንደሚነግረን የታላቋ ኢትዮጵያ ቀደምት እና ገናና ታሪክ እንደ ጠዋት ጤዛ ታይቶ የጠፋበት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም ታላቁን ድርሻ የሚወስደው ግን የእርስ በእርስ ግጭት እና ጦርነት ነው የሚሉት በርካቶች ናቸው፡፡
ጨቋኝን እንጅ ጭቆናን የማይጸየፈው ደካማ የነጻነት ባሕላችን ከነበርንበት የከፍታ ሰገነት አውርዶ ለድህነት እና ኋላ ቀርነት አጋልጦ ሰጠን እንጅ ቤዛ ሲኾነን አልታየም፡፡ ሥርዓትን ተረባርቦ መንቀል እንጅ ጠንካራ ሥርዓትን ተሠባሥቦ መትከል ያልተለማመደው የሥነ መንግሥት ባሕላችን እልፍ ጊዜ እርስ በእርሳችን አጨፋጭፎ ለውጭ ጠላት አሳልፎ ሰጠን እንጅ ጋሻ ኾኖ ሲታደገን አላስተዋልንም፡፡
ሲያልፍ መጸጸትን እንጅ ቀድሞ መንቃትን ያልተለማመደው ደካማ የፖለቲካ ተረካችን ከስሌት ይልቅ ስሜት ይበዛዋል፡፡ ሴራ እና መሳሪያ የሚወዘውዘው የአሥተዳደር ሥርዓታችን ከሰከነ ሃሳብ ይልቅ ጀብደኝነት ይፈታተነዋል፡፡
ቁጭ ብሎ መነጋገር፣ መመካከር እና በሃሳብ መሳሳብ ፍርሃት፤ አውዳሚ ጦርነት እና የእርስ በእርስ ግጭት ደግሞ ጀግንነት ተደርጎ የተሳለበት ጊዜ ሀገሪቷን በየዘመኑ ብዙ ውድ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ ነገር ግን ካለፈ ስህተታችን ዛሬስ ተምረናል ወይ? የሚለው ጥያቄ ወቅታዊ መልስ ያስፈልገዋል፡፡
በየዘመናቱ ያገኘናቸውን ጭላንጭል የሰላም አማራጮች አሟጦ ከመጠቀም ይልቅ ተስቦ እና ተሠባሥቦ ወደ ግጭት እና ፍጅት መግባት ትናንት ነበር ዛሬም አለ፡፡ ኢትዮጵያ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ስትሞክር ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ የሚጎትቷት መሰናክሎች ዛሬም ትናንት የነበራቸውን መልክ እና ቅርጽ ሳይቀይሩ ትውልድ እና ወጣት የሚገበርባቸው አረንቋዎቻችን ኾነዋል፡፡
የታሪክ እና ፖለቲካ ስብራትን የፈጠሩ ቅራኔዎቻችን ቆም ብሎ ለመጠገን ጥንስሱ ቀድሞም ቢኖርም ውይይት እና ምክክር ላይ አብዝቶ የሚሽኮረመመው ባሕላችን ሂደቶችን ሁሉ ዳር እንዳይደርሱ አድርጓቸዋል፡፡
ከዘውዳዊ አሥተዳደር ወጥታ ዘመናዊ የመንግሥት አሥተዳደርን ከተላበሰች ስድስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ምክክሮችን ለማድረግ ከአንድ ጊዜም በላይ ሁለት ሦስት ጊዜ ሞክራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ነገር ግን ሀገራዊ ቅራኔዎች እና ቁርሾዎች በትውልድ መካከል እንደ ጥላ ሞት ከኋላ ኋላ እየተከታተሉ ሲፈታተኗት ተስተውለዋል፡፡
በአሁናዊቷ ኢትዮጵያ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ስጋት እና እንቅፋት የኾኑ የሃሳብ ልዩነቶችን እና አለመግባባቶችን በውይይት እና ምክክር ለመፍታት እንዲቻል ገለልተኛ የኾነ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ በቅርቡ ከአሚኮ ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ ኮሚሽኑ በቆይታው በርካታ አበረታች ሥራዎችን ሠርቷል ብለዋል። እስካሁን የመጣበት ሂደትም ስኬታማ የሚባል ነው ይላሉ፡፡
በሀገሪቷ የዘመናት የአብሮነት ሂደት ውስጥ የሃሳብ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች መፈጠራቸው ተፈጥሯዊ ነበር ያሉት ቃል አቀባዩ ልዩነቶች ሲሰፉ ሀገራዊ መልክ መያዛቸው ደግሞ ለአብሮነት ስጋት እየኾኑ መጥተዋል ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የሃሳብ ልዩነቶችን ለመቋጨት ግጭትን የመጨረሻ እና ብቸኛ አማራጭ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ ሀገሪቷን ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡
በሀገር እና ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥ ሳንካ የሚፈጥሩ ስብራቶችን ለመጠገን ሀገራዊ ምክክር ማድረግ በክፍለ ዘመን አንድ ጊዜ የሚገኝ እድል ነው፡፡ ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጥበቡ ታደሰ በሀገራቸው ጉዳይ ይመለከተኛል የሚሉ ሁሉ ለስኬታማነቱ በቅንነት፣ በትጋት እና በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡ ይህንን እድል በአግባቡ አለመጠቀም ካለፈው እንዳለመማር የሚቆጠርም ነው ይላሉ፡፡
አሁን ላይ ኮሚሽኑ በሦስተኛው ምዕራፍ ሂደት ውስጥ ይገኛል ያሉት ቃል አቀባዩ ባለድርሻ አካላትን ሁሉ የምክክሩ ባለቤት ማድረግ በዚህ ወቅት የሚጠበቅ ዐበይት ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ ዜጎችን በምክክር ሂደቱ ተሳታፊ ማድረግ እና የአጀንዳ ሃሳቦችን የማሠባሠብ ሥራዎች እየተሠሩም ነው ብለዋል፡፡ በየደረጃው የአጀንዳ መድረኮችን ማካሄድም የሂደቱ አንድ አካል ነው ተብሏል፡፡
አሁናዊው የዓለም ሥነ መንግሥት የጸናው በደም መስመር ነው ብለው የሚያምኑ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎች አሁንም ድረስ በኢትዮጵያ ምድር አልጠፉም፡፡ ነገር ግን ይህንን የሀገራዊ ምክክር እድል ስኬታማ አለማድረግ እና በንቃት አለመሳተፍ መጻዒውን ትውልድ በአባቶቹ መንገድ እንዲጓዝ መፍረድ ነው፡፡
በአሁናዊቷ የኢትዮጵያ ምድር አዲስ የፖለቲካ እሳቤ ማጽናት ያስፈልጋል እርሱም በምክክር፣ በንግግር እና በትብብር የሚፈጠር አማካኝ ስፍራውን መቆጣጠር ነው፡፡
የሃሳብ እና ምክክር አቢዮት በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋል፡፡ በሃሳብ የፀናች እና በምክክር የቀናች ሀገር መገንባት ያስፈልጋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!