የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለወጭ ንግድ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ 25 ምርቶችን ወደ ምርት ግብይቱ ማስገባቱን ገለጸ።

50

አዲስ አበባ: ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና የላቀ የፈጠራ ሃሳብ ተግባራዊ በማድረግ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ እና አስተማማኝ የኾነ የገበያ መድረክ እና መጋዘን አገልግሎት መስጠትን ተልዕኮው በማድረግ እየሠራ ያለው የኢትዮጵያ የምርት ገበያ ድርጅት በሩብ ዓመቱ የሠራቸውን ሥራዎች በሚመለከት መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው በሦስት ወራት በተፈጸመ ግብይት ከምርት ገበያው የመግዣ ሂሳቦች ከገዥዎች ለግብይት ተቀናሽ ኾኖ ለሻጮች የተከፈለው የገንዘብ መጠን 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ሲኾን በድምሩ እስከ ጥቅምት 5/2017 ዓ.ም 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገንዘብ መንቀሳቀሱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ወንድማገኘሁ ነገራ ገልጸዋል።

በተዘረጋው የክፍያ እና ርክክብ ሥርዓት ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ሻጮች ምርታቸውን በሸጡበት ማግስት ገንዘባቸው ወደ ባንክ ሂሳባቸው እንዲገባ በማድረግ የግብይት ሥርዓቱን ፈጣን ማድረግ መቻሉን ሥራ አሥፈጻሚው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለአርሶ አደሮች የፋይናንስ ተደራሽነት እና አካታችነትን ለማረጋገጥ የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ሥርዓትን እየተገበረ ስለመኾኑም ተገልጿል፡፡

አምራቹ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዘን ምርቱን በማስገባት የመረከቢያ ደረሰኝን በማስያዥ ብድር የሚያገኝበት መንገድ መመቻቸቱንም ሥራ አሥፈጻሚው ተናግረዋል። ለሀገር የወጭ ንግድ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ 25 ምርቶችን ወደ ግብይት ሥርዓቱ በሩብ ዓመቱ በማስገባት ፈጣን እና ቀልጣፍ አገልግሎት በመስጠት ላይ መኾኑንም ሥራ አሥፈጻሚው ገልጸዋል

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በምርት ዘመኑ ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለመሠብሠብ ታቅዶ እየተሠራ ነው” የደቡብ ወሎ ዞን
Next articleድኅረ ምርት ብክነት እስከ 30 በመቶ ምርትን እንደሚቀንስ የዓለም እርሻ እና ምግብ ድርጅት አስታውቋል፡፡