
አዲስ አበባ: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የ2017 ዓ.ም የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምን በሚመለከት መግለጫ ሰጥቷል። ተቋሙ በሙሉ አቅሙ ዜጎችን ማገልገል ከጀመረ አንድ ዓመት ማስቆጠሩን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳሬክተሯ በሩብ ዓመቱ ዜጎችን በተለያየ ሙያ የሚያገለግሉ 125 ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ምሩቃንን በመመልመል በተቋሙ ዲሲፕሊን ዙሪያ አሠልጥኖ ወደ ሥራ እንዲገቡ መድረጉን ጠቅሰዋል። ተቋሙ በሦስት ወር የሥራ አፈጻጸሙ ከ400 ሺህ በላይ ቡክሌቶችን በማሳተም የመደበኛ፣ የአስቸኳይ፣ የዲፕሎማት እና የሰርቪስ ፓስፖርቶችን ለተገልጋዮች ተደራሽ ማድረጋቸውን ዋና ዳሬክተሯ ተናግረዋል።
የውጭ ዜጎችን ለመቆጣጠር እና ለማስተናገድ ቢሮው በትጋት እየሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ሩብ ዓመት በአየር ኬላ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ከሀገር የወጡ እና የገቡ እንዲሁም በየብስ ኬላ የወጡ እና የገቡ ከ230 ሺህ በላይ መንገደኞችን በመቀበል አገልግሎት መስጠታቸውን ነው ያስረዱት።
በሩብ ዓመቱ ከ250 ሺህ በላይ ቪዛ ለተገልጋዮች መሰጠቱም ተጠቅሷል። ከመጭው ጥር ጀምሮም ኢ ፓስፖርት አገልግሎት እንደሚጀመር ዋና ዳሬክተሯ ጠቅሰዋል። በቀጣይም ተቋሙ ሥራውን በቀልጣፋ መንገድ ለተገልጋዮች ተደራሽ ለማድረግ 10 ቅርንጫፎች ይከፈታሉ ነው ያሉት።
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!