
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም እየገመገመ ነው። በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ተጨባጭ የልማት ሥራዎችን እና ውጤቶችን መሥራት መቻሉን ገልጸዋል።
ከተማ እና መሠረተ ልማት ሦስት ነገሮችን ለማሳካት እንደሚሠራ የተናገሩት ኀላፊው ከተሞችን ለነዋሪዎች የተመቹ ማድረግ፣ ከተሞች ሃብት የሚፈጥሩ እና የምርታማነት ማዕከል ማድረግ እና የሥራ ዕድል የሚፈጠርባቸው ማድረግ ዋና ጉዳዮች መኾናቸውን ነው የተናገሩት። የወደፊት ዕድገት ማጠንጠኛው እና ማዕከሉ ከተማ መኾኑንም ገልጸዋል። ከተሞች ያላቸውን አቅም በመለየት የዕድገት ማዕከል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ከተሞችን የዕድገት ማዕከል ማድረግ ካልተቻለ ወደፊት ተወዳዳሪ መኾን እንደማይቻልም ተናግረዋል።
በከተሞች በርካታ ወጣቶች እንደሚገኙ የተናገሩት ኀላፊው ከተሞች ላይ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት። የከተማ ፕላን አፈጻጸም ላይ በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል። ከተሞችን ማሳደግ መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል። በፕላን የሚመሩ ከተሞች እንዲኖሩ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
የከተሞችን የወደፊት ዘመናዊነት መጠበቅ፣ በከተሞች የዘመነ አስተሳሰብ እንዲኖር እና ንጹሕ ከተማ እንዲኖር ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። የከተማ መልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን መፍታት፣ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ይጠበቃል ነው ያሉት። በከተሞች የሚስተዋለውን የመልካም አሥተዳደር ችግር ቀይ መስመር ነው ተብሎ መፍታት ካልተቻለ የኀብረተሰቡን ችግር መፍታት አይቻልም ነው ያሉት። ሕዝቡ ደንበኛ ነው በሚል በተገቢው መንገድ ማገልገል ይገባል ብለዋል።
ከኋላ ቀር የወጣ በዘመናዊ መንገድ መዋቅሮችን ማጠናከር፣ አገልግሎት አሠጣጡን የማስተካከል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። የሕግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል። በመሬት ዙሪያ ለሀገር ምሳሌ የሚኾን የአሠራር ማንዋል እየተዘጋጀ መኾኑንም ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡ ሰብዓዊነት የተላበሰ መኾን አለበት ያሉት ኀላፊው ሰው በመኾኑ ብቻ ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎት እንዲያገኝ በሰብዓዊነት ማገልገል ይገባል ነው ያሉት። ራስን በተገልጋዮች ቦታ በማስቀመጥ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል። የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
መሠረተ ልማት፣ መኖሪያ ቤት እና ኮንስትራክሽን በትኩረት እንደሚሠራባቸው ነው የተናገሩት። የቤት ልማት አማራጮችን የመጠቀም ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። ትልልቅ ፕሮጄክቶችን መቆጣጠር እና መከታተል በትኩረት የሚሠራበት መኾኑንም ገልጸዋል። በክልሉ የሚገኙ ኮንትራክተሮች እና አማካሪዎች አቅማቸው አድጎ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ተቀራርቦ መወያየት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የከተሞችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች ገቢያቸው እንዲያድግ የተሠራው ሥራ አበረታች መኾኑን ነው የተናገሩት። አረንጓዴ ልማትን እና የከተማ ግብርናን ማሳደግ ላይ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቃል ብለዋል።
የከተማ ገቢን ማሳደግ እና የኅብረተሰብ ተሳትፎን ማጠናከር በትኩረት የሚሠራበት መኾኑን ነው ያመላከቱት። በከተሞች በልዩ ትኩረት የሚሠራው አንደኛው የኮሪደር ልማት ነው ያሉት ኀላፊው የኮሪደር ልማትን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል። መንገዶችን የማስፋፋት እና የማሻሻል፣ አረንጓዴ ልማት ማልማት፣ ኅብረተሰቡ የመንገድ ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ የኮሪደር ልማቱ ዓላማዎች መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
በአማራ ክልል በ2017 የበጀት ዓመት 47 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት በከተሞች ይሠራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። በትልልቅ ከተሞች የኮሪደር ልማት መጀመሩንም አስታውቀዋል። የኮሪደር ልማት እስካሁን ድረስ የማይግባቡ ተቋማት ተግባብተው እንዲሠሩ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ተቋማትን በማቀናጀት ችግሮችን በጋራ እየፈቱ ውጤታማ ሥራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
የዲጅታላይዜሽን ሥራ ሌላው በትኩረት እየተሠራ ያለ መኾኑን ነው የተናገሩት። ለዓመታት ሲንከባለሉ የነበሩ ችግሮችን በከንቲባ ችሎቶች እየተፈቱ መኾናቸውንም ገልጸዋል። የከንቲባ ችሎት ችግርን በራስ የመፍታት አቅምን ያሳደገ፣ የሕዝብን ጥያቄ እየመለሰ ያለ መኾኑን አመላክተዋል። የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን ማጠናከር፣ በታቀደው ልክ መፈጸም እና ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!