
ባሕር ዳር: ጥቅምት 01/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአንዳንድ ነፍሰጡር ሴቶች ላይ የሚታየው ሾተላይ የሚባለው የጤና እክል ብዙ ጊዜ ጽንሱ እንዲጨናገፍ የሚያደርግ እና ከተወለደም በኋላ ቢኾን ሕጻኑ እንዳያድግ የሚያደርግ የጤና እክል ነው፡፡
ለመኾኑ ሾተላይ በጤና ባለሙያዎች እንዴት ይገለጽ ይኾን?
ሾተላይን ለማየት በሰው ልጆች ላይ የሚገኙ አራት አይነት የደም አይነቶችን መመልከት ተገቢ ነው ይላሉ የማህጸን እና ጽንጽ ስፔሻሊስት ዶክተር እስከዳር ጥላሁን፡፡ ዶክተሯ ሲያብራሩ የሰው ልጆች የሚኖራቸው የደም አይነቶች ኤ፣ ኤቢ፣ ቢ እና ኦ በመባል እንደሚታወቁ ገልጸው እነዚህ የደም አይነቶች ላይ ፕላስ እና ማይነስ የሚባሉ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
የማህጸን እና ጽንጽ ስፔሻሊስቷ ዶክተር እስከዳር ጥላሁን በቀይ የደም ሴሎቹ ላይ የሚከሰት አር ኤች ፋክተር የሚባል እንዳለ እና ፕላስ ማለት አር ኤች ፋክተር ያለው ማለት ነው። ማይነስ ማለት ደግሞ አር ኤች ፋክተር የሌለው ማለት ነው ይላሉ፡፡
አር ኤች ፋክተር ማለት በቀይ የደም ሴሎች ግድግዳ ላይ የሚከሰት ፕሮቲን ነው ሲሉም ያብራሩታል፡፡ ከዚህ በመነሳት ሾተላይ የሚያጋጥማቸው እንዴት አይነት እናቶች እንደኾኑ ሲያብራሩ አር ኤች ፋክተር የሌላቸው ማለትም ኤ ማይነስ፣ ቢ ማይነስ፣ ኤቢ ማይነስ፣ ኦ ማይነስ የኾኑ እናቶች ናቸው ይላሉ፡፡
ይህም የሚከሰተው አባትየው አርኤች ፖዘቲቭ ከኾነ፣ ማለትም ልጁ የደም አይነቱን ከአባቱ ከወረሰ ጽንሱ አር ኤች ፖዘቲቭ ፋክተር ይኾናል። ይህም ደም በጽንሱ ጊዜ ወደ እናት በሚሄድበት ጊዜ የእናት ደም እንደዚህ አይነት በአድ የኾኑ የደም አይነቶች ሲመጡ እንደጠላት ይመለከታቸዋል ነው ያሉን፡፡
በዚህ ጊዜ ይህን በአድ ነገር የሚዋጋበት ኢሚዩኖግሎብ የተባለ መከላከያ ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ብዙ ጊዜ በዚህ ሂደት የመጀመሪያ ልጅ ከኾነ በሰላም ሊወለድ ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ ይህ የእናትየዋ በአድ ነገሮችን የሚከላከልበት የሚመረተው አነስተኛ በመኾኑ የልጁን ቀይ የደም ሴል የማጥቃት ዕድሉ አነስተኛ ስለሚኾን ነው ብዋል ዶክተሯ። በዚህ ሂደት አልፎ የተወለደው ልጅ የተወሰነ ቢጫ መልክ ቢኖረውም ፀሐይ ከሞቀ አንዳንዴም እንዲሁ የማደግ ዕድሉ ሰፊ ነው ብለዋል፡፡
ችግሩ ቀጥሎ ያሉት ጽንሶች ላይ ነው የሚሉት የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስቷ ሁለተኛ እና ከዚያ በኋላ ያሉ ልጆች የማደግ ዕድል እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡
ምክንያቱን ሲያስረዱም እናትየዋ በአድ ነገሮችን የምትከላከልበት ንጥረ ነገር በብዛት ስለሚመረት እና የጽንሱን የቀይ የደም ሴል ስለሚያጠቃ ልጁ ከፍተኛ የኾነ ቀይ የደም ሴል እጥረት ስለሚያጋጥመው የመወለድ ዕድል የለውም ይላሉ፡፡
ይህ የጤና እክል እንዴት እና በምን ሁኔታ ሊታከም ይችላል?
ሕክምናው አንደኛው መከላከል ነው ይላሉ ዶክተር እስከዳር ጥላሁን፡፡ አንዲት እናት ከጸነሰች ጀምሮ ጤና ተቋም በመሄድ የደም አይነቷ ምን እንደኾነ መታወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ አር ኤች ነጌቲቨ ከኾነች የሚሰጥ ኢሚዮግሎቢን ጅ የሚባል መድኃኒት እንዳለም ነግረውናል፡፡ ይህም ከጽንሱ ወደ እናቱ የሚሄዱ ቀይ የደም ሴሎች የእናቱ የደም ሴል ሳያውቃቸው በቀላሉ እንዲጠፉ ለማድረግ የሚሰጥ መድኃኒት ነው፡፡
ብዙ ጊዜ 7 ወር ሲኾናት አንድ ዶዝ ይሰጣል፤ ይህም ለሦስት ወራት ይከላከላል፡፡ ከዚያ መልኩ እንድትወልድ ከተደረገች በኃላ የልጁ ደም አር ኤች ፖዘቲቨ ከኾነ እናቱ ሁለተኛ መድኃኒት እንድትወጋ ይደረጋል፡፡
አር ኤች ነጌቲቭ ከኾነች ግን መወጋት ሳያስፈልጋት ለሚቀጥለው እርግዝናም ተመሳሳይ ሕክምና እንደሚደረግላት ነው ያስረዱት፡፡
ሌላው የሕክምና አይነት በኢትዮጵያ ባይኖርም በተለያየ አጋጣሚ እናትየዋ ላይ መርዛማ ነገር ቢመነጭ ክትትል ታደርግ እና ችግሩ ስለመኖሩ በአልትራ ሳውንድ አማካኝነት ማወቅ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
በምርመራውም ልጁ የደም ማነስ እንዳለበት ከተረጋገጠ ልጁ ከውጭ ደም ይሰጠዋል፡፡ ልክ ማንኛውም ሰው ደም ሲያንሰው ደም እንደሚሰጠው ሁሉ ሕጻኑም በእትብቱ በኩል ደም እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡
ችግሩ ይኑር አይኑር የሚታወቀው በሕክምና በመኾኑ ነፍሰ ጡር እናቶች ሕክምና እንዲያደርጉም ዶክተሯ መክረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!