“አንድ ሚሊዮን ቶን ቡና የማምረት ግባችንን መትተናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

20

ባሕር ዳር: መስከረም 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ቡና ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዋልታ እንደኾነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቡና ልማት የታየው የዕድገት እርምጃም ይህንኑ እንደሚያንጸባርቅ ነው ያስገነዘቡት። “እጅግ አስደናቂ የኾነውን አንድ ሚሊዮን ቶን ቡና የማምረት ግባችንን መትተናል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሀገር ውስጥ የቡና ተጠቃሚነትም ትርጉም ባለው መልክ ዕድገት እንዳሳየ ነው ያብራሩት። ኢትዮጵያ ከገጠሟት ተግዳሮቶች ባሻገር በቡና ልማት ዘርፍ የበለጠ ስኬታማ መኾኗ እንደቀጠለም ነው ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ይህን ቁልፍ ኢንደስትሪ የበለጠ ለማሳደግ የየድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታት ለዕድገቱ የታየው ቁርጠኝነት ከፍ ያለ እንደኾነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም 8 ነጥብ 5 ቢሊዮን የቡና ችግኞች ስለመተከላቸው አጽዕኖት ሰጥተዋል። ለቡና የእሴት ሰንሰለት የተሳለጠ የሎጀስቲክስ አገልግሎት ወሳኝ እንደኾነ እና እሴት የመጨመር ተግባርም ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ እንደኾነ ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በቀጣይም በጠንካራ ሥራ እና ፈጠራ በመጽናት ስኬቶችን ማስቀጠል እና ማስፋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የዛሬውን በውል የምንገነዘብ እና የምንተገብር መሪዎች ነን” ይርጋ ሲሳይ
Next article”የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል ለማድረግ እንሠራለን” የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓለምአንተ አግደው