
(ልዩ ጥንቅር)
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አፈሙዞች ሰው ላይ ከማነጣጠር የሚመለሱት፣ ሰው የሚገድሉ ቃታዎች የማይፈለቀቁት፣ ምላጮች በሰው ገላ ላይ የማይሳቡት፣ ወንድም ወንድሙን ለመግደል ምሽጎች የማይቆፈሩት መቼ ነው? እናት ማልቀስ የምታቆመው፣ የመከራ ጥቁር ጨርቋን የምታወልቀው፣ እንደ በረዶ የነጣውን ቀሚሷን የምታጠልቀው፣ እንባዋን አብሳ በሳቅ የምትፍለቀለቀው መቼ ይኾን?
የደም ቦዮች የሚዘጉት፣ የመገዳደል አባዜዎች የሚቀሩት፣ ሕጻናት የጥይት ድምጽ ሳይሰሙ ውለው የሚያድሩት፣ ልጆች ያለ ስጋት የሚያድጉት፣ ወላጆቻቸውን ተነጥቀው ያለ አሳዳጊ የማይቀሩት፣ ወላጆች ያለ ሰቀቀን ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት፣ አረጋውያን ጧሪ ቀባሪዎቻቸውን በጥይት አረር የማይነጠቁት፣ ሀዘን ካጠላበት ቤት ውስጥ በችግር ከመኖር የሚወጡበት ጊዜው መቼ ነው?
ወንድም ወንድሙን የማያሳድድበት፣ ባገኘህበት ግደለው፣ ስቀለው፣ ሀብትና ንብረቱን አውድምበት፣ “ልጆቹን አግትበት” የሚሉት ሃሳቦች ቀርተው ወንድምህን እቀፈው፣ ሲዝል ደግፈው፣ ሲደክም አበርታው፣ ሲያጣ ከጎኑ ኹን፣ ከእርሱ በፊት ቅደምለት፣ ሀዘኑን አርቅለት የሚሉ ሃሳቦች የሚመጡት ከስንት ዘመን በኋላ ነው?
ደም መፋሰስ፣ አጥንት መከሳከስ አይበቃምን? ጦርነቶች የሚያበቁት ስንት ሰዎች ሲሞቱባቸው ነው? አፈሙዞች የሚመለሱት ስንት ነፍሶችን ሲጥሉ ነው? ቃታዎች የሚዘጉት ስንት ሰዎችን ከገደሉ በኋላ ነው? መቃብር እንደኾነ ሆዱ አይሞላም፡፡ የሰጡትን ሁሉ ይውጣል፤ የሰጡትን ሁሉ ያስቀራል፡፡ መቃብር ልጆቿን በበላባት ቁጥር እናት አንጀቷን አሥራ ታለቅሳለች፣ ደረቷን እየደቃች፣ ፊቷን እየነጨች አብዝታ ታነባለች፡፡
ስለምን ሰላምን ፈራን? ስለምንስ ፍቅርን ጠላን? ስለ ምንስ መገዳደልን ወደድን? ላሞች ወተት የሚሰጡት፣ በሬዎች እሸት የሚያበሉት፣ ልጆች የሚያድጉት፣ አበቦች ፍሬ የሚሰጡት፣ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱት፣ ገበያዎች የሚጠግቡት፣ የተራቡ የሚበሉት፣ የተጠሙ ጎሮሮዎች የሚጠጡት ሰላም ሲኾን አይደለምን? የደም ቦዮች የሚዘጉት፣ ወንድምና ወንድም የሚተቃቀፉት፣ የሞት ነጋሪቶች ድምጻቸውን የሚያጠፉት፣ የሞት መልእክተኞች ወደዋሻቸው የሚገቡት ፍቅር ሲኖር አይደለምን?
የታመሙት በሕክምና የሚድኑት፣ እናቶች በጤና ተቋማት የሚወልዱት፣ መንገዶች የሚሠሩት፣ ድልድዮች የሚገነቡት፣ ጎብኝዎች የሚመጡት፣ ወጣቶች ሥራ የሚይዙት፣ አረጋውያን የሚመርቁት፣ ታሪክ የሚያስተምሩት፣ ልጆች ሀገር የሚረከቡት ሰላም ሲኾን እኮ ነው፡፡
ሰላም በጠፋ ጊዜማ ሀገር የሚረከቡ ወጣቶች በጦርነት ይበላሉ፡፡ ትውልድ የሚመርቁት፣ ታሪክ የሚያስተምሩት አረጋውያን ይታጣሉ፡፡ ሰላም ከሌለማ የተሠሩ ከተሞች ይፈርሳሉ፡፡ የሚያማምሩ ውበቶች ይረግፋሉ፡፡ በአማራ ክልል አንድ ዓመት በተሻገረው ግጭት ብዙዎች ሞተዋል፣ ብዙዎች ሃብትና ንብረታቸውን አጥተዋል፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ከርመዋል፣ ተማሪዎች በማያውቁት ከእድሜያቸው አንድ ዓመት አባክነዋል፤ ብዙዎችም ተርበዋል፡፡ ተጠምተዋል፡፡ መንገድ ተዝግቶባቸው፣ ወደ ሕክምና መሄድ ሳይችሉ በቤታቸው በሕመም ማቅቀዋል፡፡ ብዙዎችም ተሳድደዋል፤ በዛቻና በማስፈራሪያ ተወልደው ካደጉበት ቀዬ ለመሸሽ ተገድደዋል፡፡
በተፈጠረው ግጭት ምክንያት መንገዶች ይዘጋሉ፣ ተጓዦች ይንገላታሉ፣ ታግተው ወደማያውቁት ሥፍራ ይወሰዳሉ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይጠየቃሉ፡፡ ያላቸው ሃብትና ንብረታቸውን፣ መኖሪያ ቤታቸውን ጭምር ሸጠው ይከፍላሉ፣ የሌላቸው ወገን አዋጥቶ እንዲከፍልላቸው ይማጸናሉ፡፡ ይሄን ማድረግ የማይችሉት ግን የውኃ ሽታ ኾነው ይቀራሉ፡፡
ከአንድ አካባቢ ወደሌላ አካባቢ በሰላም ሄዶ መመለስ ብርቅ ኾኗል፡፡ ይህም አይበቃም፡፡ ከተሞች እንቅስቃሴ እንዳይኖርባቸው፣ ጎዳናዎች ሰው እንዲናፍቁ የሚያስፈራሩም ሞልተዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሕይወትን ከባድ አድርጎታል፡፡
ታዲያ ሕዝብ ከዚህ ሰቀቀን የሚወጣው መቼ ነው? ሰላም ውሎ መግባት ብርቅ የማይኾንበትስ ከመቼ በኋላ ነው? ሀገርስ የራቃት ሰላም የሚመጣው መቼ ነው? ጦርነቱስ የሚቋጨው እንዴት ኾኖ ነው?
ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ከግጭት፣ ከወከባ፣ ከትርምስና እና ከጦርነት ተስፋ የለም ይላሉ፡፡ ተስፋ ያለው ከሰላም ነውና፡፡ በጦርነት ብሩህ የኾነ ነገር አይታይም፣ አይመጣምም፣ ሠርተን እንለወጣለን፣ ያልፍልናል የሚል ተስፋም ይጠፋል ነው የሚሉት፡፡ ጦርነቶች ተስፋን እና ሕልምን ይነጥቃሉ፣ ሕይወትንም ያጠፋሉ እንጂ ጥቅም የላቸውም፣ አንዳንድ ጊዜ ግዴታ ኾኖ አማራጭ ሲጠፋ የሚደረጉ ጦርነቶች ይኖራሉ፣ እነሱም የሀገር ክብር እና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ስለኾን እንጂ ብዙ ነገር ያሳጣሉ ነው የሚሉት፡፡ ጦርነት ያለንን የሚያሳጣ ነውም ይላሉ፡፡
በአማራ ክልል ሕዝቡ አንድ ዓመት ተሰቃየ ይበቃዋል፣ አሁን ውሳኔ ያስፈልጋል፣ ሁለቱም ወገኖች ሕዝብ ይረፍ ብለው መወሰን አለባቸው፡፡ ለዚሕ ሕዝብ ጦርነት አይጠቅምም፣ የሚያመጣው ሞትን፣ ውድቀትን እንጂ ሌላ ነገርን አይደለም ነው የሚሉት፡፡ መንገዶችን መዝጋት፣ በከተሞች እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማስገደድ ሕዝብን ያሰቃይ ካልኾነ በስተቀር ሌላ ጥቅም የለውም፤ ይህን እንደ ጀብደኝነት ወይም እንደ ትግል ስልት የሚጠቀሙ ሊኖሩ ይችሉ ይኾናል፣ ሕዝብ ግን እየተጎዳ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የኾነ፣ ጉሊትና የቀን ሥራ ሠርተው የዕለት ጉርሳቸውን የሚያገኙ ወገኖች ከተሞች ሲዘጉ ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ ይላሉ፡፡
መንገዶች ተዘግተው ሲነሰብቱ፣ ከአንደኛው ከተማ ወደሌላኛው ከተማ ነግዶ የሚበላው ሲቆም ረሃብ እየመጣ እንደኾነ ግልጽ ነው፤ ረሃብ ሲመጣ ደግሞ ሌላ ቀውስ ይጨመራል፤ ማናችንም መተንበይ ከምንችለው በላይ ጦርነቱ ከገደላቸው በላይ ረሃብ የሚገድላቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ነው የሚሉት፡፡ መንገድ ይዘጋ፣ የከተማ እንቅስቃሴ ይቁም ማለት የሚላስ የሚቀመስ የሌላቸውን ሰዎች በረሃብ ሙቱ፣ እለቁ ብሎ መፍረድ እንደኾነ ሊታወቅ ይገባልም ይላሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ለአንድ ወር ለሁለት ወር በቤቱ የሚያቆዬው የለውም፤ ሁሉም ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ ነውና፡፡
ችግሮች እየበዙ፣ ጦርነቱ እየረዘመ በመሄዱ አሁን ላይ ተስፋ እየጠፋ፣ ይህ ሲሆን ደግሞ የክልሉ ፖለቲካ የበለጠ ቅርቃር ውስጥ እየገባ ይሄዳል ብለዋል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሕዝብ ሊፈጠር ይችላል፤ ተስፋ የቆረጠ ሕዝብ ይዞ መምራት ደግሞ ውጤታማ አያደርግም ይላሉ፡፡ ሕዝቡም ከሰላም፣ ከልማት፣ ከእኩልነት ከሁሉም የተገለለ ይኾናል፤ ይህ ደግሞ አሳዛኝ ነገርን ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡ ሁለቱም ወገኖች ሕዝቡ ምንድን ነው የሚፈልገው? ብለው መጠየቅ አለባቸው፡፡ ቢያንስ ተንቀሳቅሶ እንዲሠራ መፍቀድ ይገባልም ይላሉ፡፡
ከተሞች ላይ የተመሠረተ የትጥቅ ትግል ራስን እንደማጥፋት ይቆጠራልም ነው የሚሉት፡፡ አስፈላጊው ችግሮችን በሰላም መፍታት ነው፣ ትግል ማድረግ ካስፈለገ እንኳን ከከተሞች የራቀ፣ ሕጻናትን፣ አረጋውያንን ፣ ሴቶችን ከለላ የሰጠ መኾን ይጠበቅበታል፣ ከተሞችን ከሰላማዊ ትግል ባለፈ ለጦርነት መጠቀም አውዳሚ ነው፣ ይሄን መገንዘብ ይገባልም ብለዋል፡፡
የእኛ ሃሳብ ብቻ ነው ለዚሕ ሕዝብ የሚጠቅመው፣ ከእኛ በላይ ትክክል የለም የሚል አካሄድ ችግሮችን እያባባሰ እንደሚሄድም ያስገነዝባሉ፡፡ የሃሳብ ልዩነትን ማክበር ግድታ ነው ይላሉ፡፡ የራስን ሃሳብ በሰላማዊ መንገድ ለማስረጽ መሞከር፣ ከሃሳብ የተለየውን ሃሳቡንም የሃሳቡ ባለቤትንም ማክበር ይገባል፤ ከሃሳብ የተለየውን ግን ማሳደድ አይገባም ነው የሚሉት፡፡
ጦርነት እንዲያበቃ፣ ሰላም እንዲመጣ፣ የሕዝብ ሰቆቃ እንዲያቆም ሕዝብ መረር ያለ የሰላም ግፊት ማድረግ አለበትም ይላሉ፡፡ ሁሉም ከሕዝብ ጋር ነው የሚኖሩት፣ እኛ ካልኖርን ለማን ነው የምትታገሉት? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፣ በልተን ካላደርን፣ በሕይወት መኖር ካልቻልን የእናንተ መኖር ለምን ይጠቅማል? ብሎ ሁለቱም ላይ የመጨረሻውን ጫና ማሳደር አለበት ይላሉ፡፡ አሁን በአንድ ሰውና በሁለት ሰው ውክልና ስለ ሰላም መደራደር ሳይኾን፣ ሕዝቡ በአንድ ድምጽ የሰላም ፍላጎቱን መግለጽ አለበት ነው ያሉት፡፡
ለሕዝብ ሰላም ሲባል የትኛውም ሀገር፣ የትኛውም ቦታ ይሁን ተነጋገሩ፣ የሰላም አማራጭን ተቀበሉ፣ ሕዝብ ይበቃዋል፣ የተሞከሩት የሰላም አማራጮች ካልተሳኩ ሌሎችንም አማራጮች እዩ፣ የመጨረሻውን የሰላም አማራጭ ተጠቀሙ፣ ይሄን ስታደርጉ ሞትን ታቆማላችሁ፣ ረሃብን ታስቀራላችሁ፣ ሀገርን ከትርምስ ታድናላችሁ ነው ያሉት በመልእክታቸው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!