የማኅበራዊ ሚዲያ አውታሮችን እንዴት እንጠቀም?

22

ባሕር ዳር: ነሐሴ 15/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በሚያዘወትሯቸው ማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ላይ ፈር የለቀቁ ተግባራት መበራከታቸውን እያነሱ የሚወቅሱ ጥቂቶች አይደሉም።

የማኅበራዊ ሚዲያ ሥሪቱ የብዙ ሰዎችን ሕይዎት በመልካም ሊቀይር በሚችልበት መንገድ ነበር፡፡ አሁን ላይ በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚታየው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ግን ከሥሪቱ በተቃራኒ ነው፡፡

ጥቂት የማይባሉ ወጣቶች ማኅበራዊ ሚዲያን ለመዘላለፍ፣ የግለሰቦች እና የተቋማትን ስም ለማጉደፍ እና ለሌሎች አሉታዊ ነገሮች መጠቀማቸው በጊዜ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ የሚያነሱት በርካቶች ናቸው።

የበይነ መረብ መፈጠርን ተከትሎ ማኅበረሰቡ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘዴዎችን በስፋት ይጠቀማል።

የማኅበራዊ ሚዲያን ሚና እንደ ምርቃትም እንደ እርግማንም የሚያዩትም ብዙዎች ናቸው።

ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ከተጠቀምነው ለማኅበረሰቡ ትልቅ ሚና አለው። ትልቅ የመረጃ ፍሰትን የሚያስተናግድ እንደመኾኑ ጥንቃቄ ግን ያስፈልገዋል።

በዚህ ወቅት ከፍተኛ የኾነ የመረጃ መዛባት የሚታየው በማኅበራዊ ሚዲያ ነው። መረጃን ሳያውቁ አዛብቶ ማሰራጨት እና መረጃን እያወቁም ኾን ብሎ ለጥፋት ማዛባት በዋናነት የብዙ ድሃ ሀገራት ፈተና ከኾነ ሰነባብቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያው መንደር በዝተው የሚታዩት ከመጥፎ ነገሮች ትርፍ የሚፈልጉ ሰዎች ስለመኾናቸው ያነጋገርናቸው የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት መምህር ገልጸውልናል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያዎች በተለይም በፌስቡክ እና ቲክቶክ መንደሮች በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ሽብርን የሚፈጥሩ ንግግሮች እና ልጥፎች የብዙዎችን ትኩረት ይስባሉ፡፡ እከሌ የተባለው ታጣቂ ቡድን፣ መንግሥት ወይም ሌላ አካል ‘ይሄንን አሉ’ የሚሉ የሐሰተኛ መረጃዎችም የገቢ ማግኛ ከኾኑ ሰነባብተዋል፡፡

ንትርክ፣ ዘለፋ፣ ጩኸት እና የተቀነባበሩ ዘግናኝ ድርጊቶች የበዛባቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ገበታዎች ብዙ ዕይታን የሚያገኙ ናቸው፡፡ በተለይ ከማኅበረሰባችን እሴት ያፈነገጡ ምስሎች እና ድምጾችን የሚያጋሩ ግለሰቦች በራሱ በማኅበረሰቡ ሊወገዙ ይገባል ያሉትም የዘርፉ ምሁር ናቸው፡፡

እነዚህ የመረጃ መዛባቶች ወይም መፋለሶች የሚከሰቱት አንድ ሰው ሳያውቅ እውነት መስሎት የተሳሳተ መረጃን ለማኅበረሰቡ ሲያሰራጭ ነው።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኾን ተብሎ የተዛባ መረጃ ለማኅበረሰቡ ማድረስ ነው። እዚህ ላይ የመገናኛ ብዙኅንን የመረጃ አጠቃቀም ዕውቀት ችግሩን ለመፍታት ዋነኛ መንገድ ነው።

የሚዲያ አጠቃቀም እውቀት ማለት በመገናኛ ብዙኅን ውስጥ የቀረቡ ታሪኮችን በጥልቀት የመተንተን እና ትክክለኛነታቸውን ወይም ተዓማኒነታቸውን ለይቶ የመውሰድ ችሎታ ማለት ነው።

ይህ ዕውቀት ሀገራት በስፋት እየተገበሩት ያለ እና ተመራጭነት ያለው የሚዲያ አጠቃቀም ዘዴ ነው። በተለይ ደግሞ በታዳጊ ሀገራት ላይ አስፈላጊነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው።

ምክንያቱም በነዚህ ሀገራት የሚዲያ ዕውቀት ደረጃ ዝቅ ያለ ስለኾነ ማኅበረሰቡ ለጥላቻ ንግግሮች፣ ሳያውቁ መረጃዎችን ለማዛባት እና አውቆ መረጃን ለማዛባት ችግሮች የተጋለጠ ይኾናልና ነው፡፡

ጥቂቶች ቢኾኑም የማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለበጎ ሥራ ሲጠቀሙባቸው ያየንበት አጋጣሚ አለ፡፡ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት፣ የታመሙ ሰዎችን ማሳከም እና መሰል ተግባራትን የሚፈጽሙ ሰዎች ከሐሰት ወሬ ፈብራኪዎች እኩል ተከታዮች ባይኖሯቸውም በበጎ ተግባራቸው መቀጠል ይኖርባቸዋል፡፡

ለመኾኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በአጥፊ የማኅበራዊ መገናኛ ተግባራት ላይ ለመሳተፍ ለምን ይመርጣሉ?

የሰው ልጅ በጎም ኾነ እኩይ የታመቀ ስሜት እንዳለው የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ የእርስ በርስ መስተጋብራችን የሚመጣው ይህ ስሜት የተለያዩ የማስታረቂያ ሂደቶችን (ደረጃዎችን) ካለፈ በኃላ ነው። የማኅበራዊ ሚዲያው በጣም ነጻ እና በቀላሉ የሚገኝ መኾኑ ያንን የታመቀ ስሜት አውጥቶታል ማለት እንደሚቻልም ነው የባለሙያዎቹ ገለጻ፡፡

በማኅበራዊ መገናኛዎች የአጥፊነት ባህሪያትን የሚያሳዩ ግለሰቦችን ከአዕምሮ ሕመም ጋር የማገናኘት ፍረጃ ግን ተገቢ እንዳልኾነ ባለሙያዎቹ ይሟገታሉ። አሁን ያለው ዓለማዊ ኹኔታ ሰዎች ራሳቸውን መቆጣጠር የሚችሉበትን ሥነ አዕምሯዊ ኹኔታ እየፈተነው እንደኾነ ግን የባለሙያዎቹ እምነት ነው።

ከዚሁ የባለሙያዎች ሐሳብ በመነሳት አንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያን በአሉታዊ ጎኑ የሚጠቀሙ ሰዎች በጤና እክል ወይም ሐሳባቸውን የሚያጋሩበት መንገድ አጥተው ሳይኾን ከመጥፎ ድርጊታቸው የሚያገኙት ጥቅም ስላለ መኾኑን መረዳት ይቻላል፡፡

ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች በማኅበራዊ ሚዲያ የተሳሳቱ መረጃዎች አማካይነት የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ማቆም እና የንግድ ተቋማት መዘጋት አጋጥሟል፡፡

እነዚህ የተዛቡ መረጃዎች በብዙ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ማስከተላቸውም የአደባባይ ሃቅ ነው፡፡ ጥያቄው ከእነዚህ እኩይ ተግባራት አትራፊው ማነው? የሚለው ነው፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያን ተከታይ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚሰራጩ የተዛቡ መረጃዎች ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፤ መረጃን አጥርቶ ማሰራጨትም የስልጡንነት ማሳያ ነው ሲሉ የዘርፉ ሙያተኞች መክረዋል፡፡

በኛ ሀገር የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝብን ነባር እሴቶች የሚሸረሽሩ፣ የሀገር አንድነትን የሚንዱ፣ ዘረኝነትን የሚሰብኩ እና ሌሎች አሉታዊ ነገሮች የሚንጸባረቁባቸው ስለኾኑ መጠንቀቁ የሁላችንም ድርሻ ሊኾን ይገባዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleኅብረተሰቡን ያሳተፈ የበሽታዎች ቁጥጥር እንዲከናወን ተጠየቀ፡፡
Next article