
ደብረ ብርሃን: ነሐሴ 14/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሥራ እንቅስቃሴ በሚመለከት በደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል። ከሥራ ዕድል ፈጠራ እና ተኪ ምርቶችን ከማምረት ጎን ለጎን ኢንዱስትሪ ፓርኮች የዕውቀት ሽግግር እና ማኅበረሰባዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ይጠበቃል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች እና መሠረተ ልማት ዘርፍ አሥተባባሪና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።
በተለይ ደግሞ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀራርበው መሥራት አለባቸው ያሉት ኀላፊው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዕውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ ይጠበቃል ነው ያሉት። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ዓለማየሁ ሰይፉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዚህ በፊት የነበራቸውን እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለሃብቶችን ተጠቃሚ የሚኾኑበት ዕድል በመፈጠሩ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባው የደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ እስካሁን ከ7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱን የተናገሩት ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ የሺጥላ ሙሉጌታ ናቸው።
ዘጋቢ፡- በላይ ተስፋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!