እንወድሃለን የሚሉትን ሕዝብ ማሸበር ለማን ይጠቅማል?

59

ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝብ የሚያስደነግጠው፣ የሚያስጨንቀው፣ ሰላም የሚነሳው፣ እኔ ስፈቅድ ውጣ፣ እኔ ሳልፈቅድ አትውጣ የሚለውን ይፈልጋልን? መንገድህን በእኔ ቸርነት እከፍትልሃለሁ፣ እኔ ካልቸርኩ እዘጋዋለሁ የሚለውንስ ይወዳልን? መንገድህን ለአምላክህ ስጥ ብሎ አምላኩን ተማምኖ ከቤቱ የሚወጣውን ሕዝብ ስነ ልቦና መጋፋት አይሆንምን? እንጨት ሸጣ ልጆቿን የምታጎርስ፣ ቀዳዳ ቀሚሷን ሰፍታ ልጆቿን የምታለብስ እናትን ገበያ እንዳይኖራት፣ ከመቀነቷ ሳንቲም እንዲያጥራት ማድረግስ የተገባ ነውን?

ባገኘህበት ግደለው፣ ባገኘህበት ስቀለው፣ ባገኘህበት ውሰደው፣ ሃብትና ንብረቱን ቀማው፣ እምቢ ካለ ባለበት አውድመው ማለትስ የተገባ ነው ወይ? እርሱ ይሙት ልጆቹን ማን ያሳድጋቸው? ማንስ አለሁ ይበላቸው? ማንስ ይሰብስባቸው? ልጆቹ እኮ ይፈልጉታል፤ ወጥቶ እስኪገባ እኮ ይናፍቁታል፡፡ ግደለው ሲባል ስለ ምን ይገደላል? ስለ ምን ይሰቀላል? ብሎ አለመጠየቅስ ጤነኝነት ነውን? ተው ይሄን ነገር አይበጅም የሚልስ እንዴት ጠፋ?
ከተሞችን ዝጉ፣ ሥራችሁን ጥላችሁ ውጡ፣ ሲንቀሳቀስ የተገኘ እርምጃ ይወሰድበታል፣ ሃብቱ ይነጠቃል፣ እርሱም ይገደላል እያሉ ማሸበር፣ ማስፈራራት፣ ሠርቶ የሚበላውን ሥራ ማስፈታትስ የተገባ ነው ወይ? አይዟችሁ ሥሩ፣ ኑሯችሁን ለውጡ፣ ልጆቻችሁን አሳድጉ፣ ሰላማችሁን ጠብቁ ማለት አይሻልምን? የሚጠቅመው እንወድሃለን የሚሉትን ሕዝብ ማሸበር ወይስ ማረጋጋት?

“ዋሽታችሁ አስታርቁ” የሚል ብሒል ባለው ሕዝብ መካከል ወጥቶ ዋሽቶ ማጣላት፣ ዋሽቶ ማጋደል፣ ዋሽቶ ሕዝብ የሚመላለስባቸውን ጎዳናዎች ማዘጋት፣ በከተሞች የሞት ነጋሪት ማስጎሰም፣ ያለ እረፍት ሠርተው ኑሮ አልቻል ያላቸውን ወገኖች ሥራ ማስፈታት፣ በችግር ማሰቃየት፣ የቀን ሥራ ሠርተው የእለት ጉርስ ለልጆቻቸው ይዘው የሚገቡትን ከተማ ዘግቶ በቤት ውስጥ እንዲውሉ ማድረግስ ተገቢ ነውን? ከአባትና ከእናታቸው እጅ የእለት ጉርስ የሚጠብቁ ሕጻናት ረሃብ አያሳዝንምን? ወይስ ረሃብን አታውቁትምን? ረሃብ ስንት ቀን ያቆያል? የሚለውን የአበውን ጥያቄስ የሚያውቅ የለምን?

የትግል መንገዱ፣ ለሕዝብ መቆርቆሩ፣ የጀግንነት መለኪያው ከተሞችን በማሸበር፣ የአርሶ አደሮችን ጓዳ በመበርበር፣ ከራስ ሃሳብ በታቃራኒ ያለውን ሁሉ መግደል ነውን?
የሽማግሌ በትር በማይዘለልበት፣ ሁለት ጸጉር ያበቀሉ አበው መንገድ በማይቋረጡበት፣ የሃይማኖት መሪ እንደ አምላክ በሚከበርበት፣ በባንዲራው አምላክ ሲባል ጥልና ጥላቻ በሚቆምበት፣ ለበቀል የዞረች አፈሙዝ በምትመለስበት፣ በንጉሡ አምላክ በተባለ ጊዜ ለሞት የተፈላለጉ ሰዎች ለሰላም እጃቸውን በሚዘረጉበት ሕዝብ ውስጥ ወጥቶ ሽማግሌን መድፈር፣ የሃይማኖት አባትን ማወረድ እና ማሳደድስ ለሕዝብ መቆርቆር ነውን? እሴትን፣ ባሕልንና ሃይማኖትን መጣስ አይኾንምን?

ታረቁ ብለው የሄዱ ሽማግሌዎችን ማሰቃየት፣ ገንዘብ ካልሰጣችሁን ወደ ቤታችሁ አንመልሳችሁም ብሎ ማገት፣ ከኔ በተቃራኒ ቆማችኋል ጠርጥሬያችኋለሁ ብሎ መግደል፣ በእድሜና በችግር ለጎበጠው ወገባቸው ምርኩዝ ማቀበል ሲገባ ሕዝብ በተሰበሰበበት አንበርክኮ አንበሳ ገዳይ እያሉ እየጨፈሩ መንዳትስ መልካምነት ነውን?

ያልታደለች ሀገር በዚህ ዘመን ዋሽተው ከሚያስታርቋት ዋሽተው የሚያጋጯት፣ ሰላምን ከሚያመጡላት ሰላም የሚነሷት፣ ጎዳናዎቿን ከሚሠሩላት ጎዳናዎቿን የሚዘጉባት በዝተውባታል፡፡ ሰላምን የሚሰብኩት እንደ ፈሪ፣ እንደ ባንዳ፣ እንደ ተላላኪ ይቆጠራሉ፡፡ ግደለው፣ መንገዱን ዝጋው፣ በከተማ እንቅስቃሴ እንዳይኖር እያሉ የሚለፍፉት ጀግና ተብለው ይወደሳሉ፡፡ የሀሳብ ልዩነትን ማክበር ስለ ምን ጠፋ? አሁን ሀገር ወሬ የሚፈታት፣ ውሸት የሚንጣት ኾናለች፡፡
እሴት እና ሥርዓት ያላት ሀገር አልመስል ብላለች፡፡ በሥርዓት ከመመራት ይልቅ በሁከት የሚናጠው በዝቷል፡፡ የቀደሙት ሰዎች ወሬ በወሬ ተሰማምተው ሰላማቸውን ይጠብቃሉ፡፡ የዚህ ዘመኖቹ ደግሞ ወሬ ሰምተው ከተሞቻቸውን ይዘጋሉ፣ ሐሰተኛ መረጃ ወስደው ሥራቸውን ያቆማሉ፡፡ በራቸውን ቆልፈው በማኅበራዊ ሚዲያ ውጡ እስከሚባሉ ድረስ ይጠብቃሉ፡፡ ስለምን ለወሬ ጆሮ መስጠት ማቆም አልተቻለም? ስለ ምንስ በቃን ሰላማችን እንሻለን፣ ሠርተን መብላት እንፈልጋለን፣ እንኳን ከፎከረ ከወረወረ ያድናል የሚለው ብርቱ ስነ ልቦና የት ደረሰ? ሐሰተኛ ወሬ የማይንጠው ብርቱ ማኅበረሰብ ለምን ጠፋ?

ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት ውስብስብ ችግሮችን አምጥቷል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት በብዙ ቢሊዮኖች ብር የሚገመት ሃብትና ንብረት ያጣው፣ በርካታ ነዋሪዎቹን የተነጠቀው ክልል ከችግር ሳይወጣ ሌላ ችግር ገጥሞት ሃብትና ንብረት ወድሟል፡፡ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ተገድቧል፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ከትምህርት ገበታቸው ርቀዋል፣ እናቶች በመደብ ተኝተው እንዲወልዱ ተገደዋል፤ ልጆች ወላጆቻቸውን ሳይቀብሩ ቀርተዋል፡፡ነጋዴዎች ሥራቸውን እየተዉ ከተማ ለመቀየር ተገድደዋል፡፡ ባለሀብቶች በስጋት ጥለው ተሰድደዋል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚጓዙ ተማሪዎች የወላጆቻቸውን ቀንጃ በሬ ሸጠው የአውሮፕላን ትኬት ገዝተዋል፡፡ ጥረው ግረው ኑሮን ለመቆጣጠር ይደክሙ የነበሩ አሁን ኑሮን ለመቋቋም ተቸግረዋል፡፡

አሁንም መንገዶቹን ይዘጋሉ፤ ከተሞች እንዲዘጉ ማስፈራሪያዎች ይደርሳሉ፡፡ የክልሉ ዋና ከተማ ባሕርዳርን ጨምሮ ሌሎች ከተሞች እንዲዘጉ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች እየደረሱ ነው፡፡ ከሰሞኑ በባሕርዳር ከተማ በተነዛው ማስፈራሪያና ዛቻ እንቅስቃሴ ቆሞ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በፍጥነት ወደ ነበረበት እንቅስቃሴ ቢመለስም፡፡ ይህ ደግሞ ኑሮ ያጎበጠውን፣ ተደራራቢ ችግር ያማረረውን የክልሉን ሕዝብ መከራውን አጥንቶበታል፤ በከተማ ያለው በገጠር የተመረተውን አያገኝም፣ በገጠር ያለው በከተማ የሚፈልገውን አይወስድም፡፡ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ፣ ሥራ ተረጋግቶ እንዳይሠራ እያደረገው ነው፡፡

ግጭቶች ካልቆሙ ሁሉም ሰላምን ካልሰበከ፣ ለሰላም ካልሠራ፣ ውሸቶችን በእውነት እየጣለ እስካልሄደ ድረስ የክልሉ ሕዝብ በፖለቲካ እና በምጣኔ ሃብት መወዳደር ብርቅ ይኾንበታል፤ ለመኖር ይቸገራል፡፡
እናም ሁሉም ሰው የሚጠቅመውን ከማይጠቅመው ነጥሎ ማየት፣ በሚዛን መኖር፣ ሕዝብና ሀገር የማይጎዱበትን አካሄድ መምረጥ ግድ ይላል፡፡ መስከን፣ መረጋጋት፣ ነገን ማሰብ፣ ከራስ በላይ ለሌሎችም መጨነቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልኾነ ግን አኗኗራችን ይከፋል፡፡ ሰው በሰው ይጠፋፋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአማራ ባንክ በ2016 በጀት ዓመት ከ377 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
Next articleበፀጥታ ችግር የቆሙ የልማት ጉድለቶችን የሚሞላ ሥራ እየተሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ገለጸ፡፡