“ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት”

59

ባሕር ዳር: ነሐሴ 13/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቡሔ የክረምቱ ጨለማ ተገፎ የብርሃን ወጋገን የሚታይበት ወቅት ነው። ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት ክረምት ከበጋ የሚሸጋገሩበትም ነው፡፡ ለዚህም ነው “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” የሚባለው ሲሉ የታሪክ መምህር ሙላት ዓይኔ የተናገሩት።
የቡሔ በዓል በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ክዋኔዎች ይከበራል።

“ማን ይናገር የነበረ፤ ማንያርዳ የቀበረ” እንዲሉ ወይዘሮ እርጎዬ ማማሩ በባሕር ዳር ዙሪያ እና በደቡብ ጎንደር ኩታ ገጠም በኾነው የወንቅሸት ገብርኤል አካባቢ ነዋሪ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት ክረምቱ ሲገባ ቡሔ በስስት የሚጠበቅ እና የሚናፈቅ በዓል ነው። በእነርሱ አካባቢ ለቡሔ እናቶች ቀደም ብለው ይዘጋጃሉ። ጎተዋ/ጎተራዋ/ የተሟጠጠ፣ መቀነቷ የደረቀ እናት እንኳ ለቡሔ ተበድራም ቢኾን ትዘጋጃለች።

ወይዘሮዋ እንዳሉት ለቡሔ እማዎራዎ/አባዎራው ስንዴ ወይም በቆሎ አሊያም ጤፍ ቀደም ብለው ያስፈጫሉ። በቡሔ ዋዜማም በርካታ ሙልሙል ዳቦ ይጋገራል። “ቡሔ በሉ !” ብሎ ለመጣ ሁሉ ዳቦ ያለሥሥት ይሰጣል። ለጎረቤት እና ለዘመድም እንዲሁ ይበረከታል ነው ያሉት።

በቡሔ ዕለት የቆሎ ተማሪ “ስለ እመ ብርሃን” ለማለት ከጎጆው ሲወጣ ነጭ ጥምጣም ጠምጥሞ ቀጭን ዘንግ ይዞ ሲኾን ያልተቆረሰ ዳቦም ይሰጠዋል ብለዋል።
ሕጻናት በ”ቡሔ” ዳቦ ባይሰጣቸውም “ደግሞ ለከርሞ በሰላም ያድርሳችሁ!” ይላሉ እንጅ ክፉ ነገር ከአንደበታቸው አይወጣም ሲሉ ነው ወይዘሮ እርጎዬ የተናገሩት።
“በቡሔ ሰሞን እረኞች በመስክ ከብት ሲጠብቁ አርሶ አደሮች በማሳ እርሻ ሲያርሱ እና አረም ሲያስወግዱ ለምሳ የሚወስዱት ሙልሙል ዳቦ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

ለቡሔ በተጠመቀ ጠላ ወይም አረቂ፣ ለቡሔ ተብሎ በተፈጨ ዱቄት እንጀራ እየተጋገረ ሰብላቸውን በወበራ (በደቦ/በወል እና ወንፈል ) እርሻ በማረስ ወይም አረምን በማስወገድ ሰብልን ለመንከባከብ በዓሉን አስበው መልካም ነገር እንደሚከውኑበት ነግረውናል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የደብረ ታቦር ነዋሪው አቶ ደጀን መብሬ ደግሞ በቡሔ በዓል የሰፈር ሕጻናት ተሠባሥበው በየቤቱ እየዞሩ “ቡሔ! ቡሔ! ቡሔ!” እያሉ ይጨፍራሉ። በዚህ ጊዜም እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሱ ይሰጣሉ ነው ያሉት።

ወደ ገጠሩ አካባቢ ታዳጊዎች ጅራፍ በመግረፍ በዓሉን እንደሚያከብሩትም ተናግረዋል።
በበዓሉ ዋዜማ ምሽት ላይ ችቦ (ጠንቦራ) በማብራትም እንደሚከበር ነው አቶ ደጀን የነገሩን።
ይህም የሚደረገው ደብረ ታቦር ተራራ ላይ ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ እንደኾነ ሲወርድ ሲወራረድ መስማታቸውን ነው ያስረዱት።

“በእኛ ቤት በቡሔ ዕለት ቡሔ ከሚሉት በተጨማሪ ከሚዘጋጀው ዳቦ ለጎረቤትም ይሰጣል። በተለይ በቡሔ ዕለት እኔ እና ባለቤቴ የክርስትና ልጆቻችን ቡሔ ብለው ሲመጡ ከዳቦ በተጨማሪ ልዩ ስጦታ እንሰጣቸዋለን። ለጡት ልጅም ሥጦታ ይበረከታል። ለአማች እና ለምራትም የቡሔ ዳቦ ተዘጋጅቶ ይዘከራል” ነው ያሉት።

ከደቡብ ጎንደር ወደ ባሕር ዳር ዙሪያ ስንመለስ ቡሔ በወረዳው በሚገኙ በተለይ በፈረስ ወጋ፣ በግንብ ጊዮርጊስ፣ በቅንባባ፣ በማቋል፣ በድንጋይ ደበሎ ማርያም፣ በአንዳሳ ጊዮርጊስ አካባቢዎች የሚያከብሩት የቆሎ ተማሪዎች እንደኾኑ በመስኩ ለሁለተኛ ዲግሪያቸው የማሟያ ጥናት የሠሩት የታሪክ ምሁር ሙላት አይኔ ነግረውናል።
መምህር ሙላት ጨምረው እንዳሉት የቆሎ ተማሪዎች የቡሔ በዓልን በድምቀት ነው የሚያከብሩት።
ለዚህም ቀደም ብለው የእንጀራ እና የዳቦ ዱቄት እንዲሁም ለንፍሮ የሚኾን ጥራጥሬ በመለመን ይዘጋጃሉ።

ይህንንም እንጀራ እና ዳቦ በመጋገር እንዲሁም ንፍሮ በማንፈር የበዓሉ ዕለት ዕምነቱ የሚያዘውን የተነደፈ ጥጥ የመሰለ የክት ልብስ ለብሰው፣ ነጭ ጥምጣም በሦሥት ደረጃ በመጠምጠም፣ ነጭ ነጠላቸውን ትምዕርተ መስቀል በመጎናጸፍ ቤተ ክርስቲያን ለመሳም የመጣውን አማኝ ሁሉ የደብረ ታቦርን ስም እየጠሩ፣ ቡሔን እያወደሱ፣ እየዘመሩ ያዘጋጁትን ምግብ በመቃመስ ሐሴት ያደርጋሉ። አማኙም “እንዳከበራችሁን ክበሩልን! እንደዘንድሮም በሰላም እንገናኝ ከርሞም” እያሉ እንደሚመርቋቸው መምህር ሙላት ነግረውናል።

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ

Previous article“የዘመን ኮከቦች፣ ታላቅ ሀገር አውራሾች”
Next articleየ2017 የበጀት ዓመት የፀጥታ እና የልማት ሥራዎችን አስተሳስሮ በመፈፀም ዞኑን ወደ ተሟላ ሰላም ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ ተመላከተ።