“ኢትዮጵያውያን በመተባበር በአንድ ጀምበር ለመትከል ከታሰበው በላይ በማሳካት ሀገራችንን ማስጠራት አለብን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ

21

ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን በመተባበር በአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለመትከል ከታሰበው በላይ በማሳካት ሀገራችንን ማስጠራት አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ነሐሴ 17 በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር 600 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አሻራችንን እናኑር በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዚህም አዋቂዎች ከ20 በላይ፣ ታዳጊወች ከ10 በላይ ችግኞች በመትከል ለሀገር ያለንን ፍቅር፣ ለትውልድ ያለንን ስጦታ በተገቢው ስፍራ እንግለጥ ብለዋል።

አንድ ከሆንን ከዚህም በላይ እንችላለን፤ በአንድ መንፈስ በመላው ኢትዮጵያ አሻራችንን እናኑር ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወቃል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር በተገቢው መንገድ እንደቀጠለ ነው ብለዋል።

በዚህም በዘንድሮው ዓመት ለመትከል ከታቀደው 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ውስጥ ከ6 ቢሊየን በላይ መተከሉን ገልጸዋል።

የአንድ ጀምበር መርኃ-ግብርን ጨምሮ በቀሪ ጊዜያት የዓመቱን ዕቅድ ማሳካት ሲቻል ባለፉት ዓመታት የተተከለውን ጨምሮ በአጠቃላይ በመርሃ ግብሩ የተተከሉ ችግኞች ብዛት ወደ 40 ቢሊየን እንደሚደርስ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ለአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ችግኞችን በብዛት መትከል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በመተባበር በአንድ ጀምበር ለመትከል ከታሰበው በላይ በማሳካት አገራችንን ማስጠራት አለብን ብለዋል።

ነሐሴ 17 በሚካሄደው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ኢትዮጵያውያን በንቃት በመሳተፍ አሻራቸውን እንዲያኖሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በ2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርኃ-ግብር ከ566 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸው ይታወሳል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያበረታታ ከባቢ ይፈጥራል” አቶ አሕመድ ሽዴ
Next articleበአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችውን የሕጻን ሄቨንን ጉዳይ እየተከታተለው መኾኑን የሴቶች አና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለጸ።