የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያበረታታ ከባቢ ይፈጥራል” አቶ አሕመድ ሽዴ

22

ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያበረታታ፣ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እና ተገማች የቢዝነስ ከባቢ እንደሚፈጥር የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገልጸዋል።

በአይሻ አንድ የነፋስ ኀይል ማመንጫ በ620 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር 300 ሜጋ ዋት ኀይል ማመንጨት የሚያስችል ሥምምነት ተፈርሟል።

የትግበራ ሥምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እና የአሚአ ፖወር ሊቀ መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ ተፈራርመዋል።

በተመሳሳይ አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኀይል ማመንጫ የሚያመነጨውን ኀይል ለኢትዮጵያ ለመሸጥ የኩባንያው ሊቀ መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተፈራርመዋል።

ተቀማጭነቱን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ያደረገ በታዳሽ ኀይል ልማት፣ ግንባታ እና አሥተዳደር ዘርፍ የተሰማራው አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኀይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት በማመንጨት ለ25 ዓመታት ለኢትዮጵያ ለመሸጥ ነው ሥምምነቱን የፈጸመው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ20 በላይ በሚኾኑ የዓለም ሀገራት በታዳሽ ኀይል ዘርፍ የተሰማራው አሚአ ፓወር አይሻ አንድ የነፋስ ኀይል ማመንጫን ሙሉ በሙሉ በራሱ በመገንባት ያመነጨውን ኀይል ለኢትዮጵያ እንደሚሸጥ ነው በመድረኩ የተገለጸው።

ፕሮጀክቱ ከአራት ሚሊዮን በላይ ቤተሰብ የኀይል ተጠቃሚ ከማድረጉም ባለፈ በዓመት ከ690 ሺህ ቶን በላይ የበካይ ጋዝ ልቀትን ይቀንሳል ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሰማሩ ኩባንያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ፍላጎታቸው እያደገ መጥቷል።

ለዚህም በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ሁሉን አቀፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ውጤት መኾኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ገቢራዊ ያደረገችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ለሚፈልጉ የውጭ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በጋራ እየሠሩ መኾኑን ገልጸው ከአሚአ ፓወር ጋር የተደረገው ሥምምነት ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማሳያ ነው ብለዋል።

የአይሻ አንድ የነፋስ ኀይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአፍሪካ የአረንጓዴ ኀይል ሽግግር በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ማሳያ እንደኾነም አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱ የማኅበረሰብ ልማትን በማቀላጠፍ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማሳደግ እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመፍጠር ለሀገር ውስጥ እና ለቀጣናው ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።

የአሚአ ፓወር ሊቀ መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ “ፕሮጀክቱን ገቢራዊ ለማድረግ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና መንግሥት ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ ነን” ብለዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ የአይሻ አንድ የነፋስ ኀይል ማመንጫ በአፍሪካ ቀንድ ግዙፉ መኾኑን ጠቅሰው ከኢትዮጵያ ጋር እንደዚህ አይነት ሥምምነት መፈራረማቸው ልዩ እንደሚያደርገውም አስረድተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበመንግሥትና በሕዝብ ኃብት ላይ ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ያደረሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራቸው እየተጣራ መኾኑ ተገለጸ።
Next article“ኢትዮጵያውያን በመተባበር በአንድ ጀምበር ለመትከል ከታሰበው በላይ በማሳካት ሀገራችንን ማስጠራት አለብን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሥገን ጥሩነህ