በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ።

21

ባሕር ዳር: ነሐሴ 11/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በ620 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር 300 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ።

የትግበራ ሥምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴና የአሚአ ፓወር ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ ተፈራርመዋል።

በተመሳሳይ አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ የሚያመነጨውን ኃይል ለኢትዮጵያ ለመሸጥ የኩባንያው ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ተፈራርመዋል።

ተቀማጭነቱን በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ያደረገ በታዳሽ ኃይል ልማት፣ ግንባታና አሥተዳደር ዘርፍ የተሰማራው አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት በማመንጨት ለ25 ዓመታት ለኢትዮጵያ ለመሸጭ ነው ሥምምነቱን የፈጸመው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ20 በላይ የዓለም ሀገራት በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የተሰማራው አሚአ ፓወር፣ በአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫን ሙሉ በሙሉ በራሱ በመገንባት ያመነጨውን ለኢትዮጵያ እንደሚሸጥ ነው በመድረኩ የተገለጸው።

ፕሮጀክቱ ከአራት ሚሊየን በላይ ቤተሰብ የኃይል ተጠቃሚ ከማድረጉም ባለፈ በዓመት ከ690 ሺህ ቶን በላይ የበካይ ጋዝ ልቀትን ይቀንሳል ተብሏል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በጋራ እየሠሩ መኾኑን ገልጸው ከአሚአ ፓወር ጋር የተደረገው ሥምምነት ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማሳያ ነው ብለዋል።

የአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በአፍሪካ የአረንጓዴ ኃይል ሽግግር በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ማሳያ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የማኅበረሰብ ልማትን በማቀላጠፍ፣ የኢንዱስትሪ አብዮትን በማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በመፍጠር ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሚአ ፖወር ሊቀ-መንበር ሁሴን አል ኖዋይስ፣ ፕሮጀክቱን ገቢራዊ ለማድረግ ከአካባቢው ማኅበረሰብና መንግሥት ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ ነን ማለታቸውን ኢዜአ ዘገቧል።

የአይሻ አንድ የነፋስ ኃይል ማመንጫ በአፍሪካ ቀንድ ግዙፉ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንደዚህ አይነት ሥምምነት መፈራረማችን ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻና አማራጭ በመሆኗ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እናደርጋለን ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየድሬዳዋ አሥተዳደር የምክክር ተሳታፊዎች አጀንዳዎቻቸውን ለኮሚሽኑ አስረከቡ።
Next articleየተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን ከማኅበረሰቡ ጋር በትብብር እየሠራ መኾኑን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አስታወቀ።