ከጦርነት እስከ ክትባት የዘለቀው የቅኝ ግዛት እሳቤ ውልድ፡፡

231

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 02/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከጦርነት ጉሰማ እስከ መድኃኒት ቅመማ እና ከባሪያ ንግድ እስከ አፓርታይድ የዘለቀው የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ ውልድ ዛሬም ድረስ እስከ ወቅቱ የዓለም አስከፊ የኮሮና ድረስ ዳፋው ዘልቋል፡፡ ዓለም በዚህ ሰዓት ከሕክምና እስከ ምሕላ ጸሎጽ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እና ለመቆጣጠር የምታደርገውን ጥረት የሚፈታተኑ ሁለት ዐበይት ክስተቶች ከሰሞኑ ብቅ ብለዋል፡፡

የነጩ ቤተ መንግሥት ፊታውራሪ እና የልዕለ ኃያሏ አሜሪካ መሪ ‘‘የቻይና ቫይረስ’’ ሲሉ የዳቦ ስም ያወጡለትን የኮረና ቫይረስ ሀገራው በአንድ መዓልት እና ሌሊት ጠራርጋ እንደምታስወጣው ቢዝቱም እየሆነ ያለው ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ ይህንን ድክመታቸውን ለመሸፈን ሲሉ ደግሞ ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር ‘‘የእናቴ ቀሚስ ጠለፈኝ’’ ሰበብ ፍለጋ እስጣ አገባ ገጥመዋል፡፡ በምርጫ ዋዜማ ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወረርሽኙ አደገኛ ሆኖ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ከመግለጽ ይልቅ የዓለም ጤና ድርጅትን መኮነን ጀምረዋል፤ ‘ባለንጀራው ቢያጠቃው …’ እንዲል የአገሬ ሰው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ‘‘የኮሮና ቫይረስ ክትባት በአፍሪካውያን ላይ ሊሞከር ይገባል’’ ያሉት ሁለት የፈረንሳይ ተመራማሪዎች ንግግር የዓለም ጥቁር ሕዝቦችን ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ ሁለቱ ርእሰ ጉዳዮች ዓለም በጋራ ቁማ ልትከላከለው ይገባል እየተባለላት ያለውን ወረርሽኝ ትኩረት እንዳይቀለብሱት የሚሰጉትም በርካቶች ናቸው፡፡

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሁለት የፈረንሳይ ተመራማሪዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት በአፍሪካውያን ላይ ሊሞከር ይገባል ማለታቸውን ተከትሎ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጥቁሮች ክፉኛ ተቆጥተዋል፡፡ ነገር ግን የአልጀዚራውን ጦማሪ ካርስቴን ኖኮን ጨምሮ በርካቶች ደግሞ ይህንን የጥቁር ሕዝቦች ብስጭት ‘‘ምን አዲስ ነገር ተፈጠሮ ነው?’’ ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ‘‘እሳቤው የነበረና ያለ ነው’’ ሲሉ ታሪካዊ ማጣቀሻዎችን ሲያቀርቡም ‘‘አስተሳሰቡን የባሪያ ንግድ እና የቅኝ ግዛት እሳቤ ውልድ ነው’’ ይሉታል፡፡

ባለፈው ታኅሣስ አካባቢ በቻይና የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት ሁሉንም የዓለም ሀገራት እያዳረሰ ይገኛል፡፡ ‘‘በዓለም ላይ ያሉ የሕክምና ልሂቃን መፍትሔ በማፈላለግም ላይ ናቸው’’ ያለው የአልጀዚራው ጦማሪ ካርስቴን ኖኮ የፈረንሳይ ተመራማሪዎቹ የመፍትሔ ሐሳብ የተወለደውም ጥቁሮች በቫይረሱ እምዛም አይጠቁም ከሚለው የተሳሳተ መላምት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‘‘ተቀራራቢ የሆነ ሥነ ሕይወታዊ ሥሪት ባለው የሰው ልጅ ላይ እንዲህ የቆዳ ቀለምን መሠረት ያደረገ የመፍትሔ ሐሳብ ይዞ መቅረብም ምንጩ ታሪካዊ የአፓርታይድ አስተሳሰብ ስሪት ነው’’ ሲልም ይሞግታል፡፡

መሰል ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በሕክምናው ዘርፍ መታየት የጀመሩት ከ1810 (እ.አ.አ) ጀምሮ እንደሆነ ያስታወሰው ኖኮ በወቅቱ ደቡብ አፍሪካዊቷ ሳራ ባርትማን በነበራት ግዙፍ ተክለ ሰውነት እና ትልቅ ዳሌ የተገረሙት ነጮቹ ወደ አውሮፓ ሀገራት ተወስዳ ክብረ ነክ በሆነ መንገድ ለበርካት ሕዝብ ለዕይታ (ኤግዚቪሽን) ቀርባ እንደነበር በማስረጃነት አቅርቧል፡፡ በወቅቱም ‘‘ሳራ ሰው ሳትሆን ሰው መሰል እንስሳ እንደሆነች በመቁጠር ሕይወቷ ሲያልፍም አፅሟ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመለሶ (በ2002 እ.አ.አ) በክብር እስኪያርፍ ድረስ ለ150 ዓመታት በፈረንሳይ ብሔራዊ ሙዚዬም ተቀምጦም ነበር’’ ይላል፡፡

ለምዕተ ዓመታት የዘለቀው ጥቁርን የበታች የሚያደርገው የነጮች ዘረኛ አስተሳሰብ እስካለንበት ዘመን ድረስ መልኩን እየቀየረ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ በ2014 (እ.አ.አ) በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በተከሰተው የኢቮላ ወረርሽኝ ወቅት ከ250 ሺህ በላይ ጥቁሮች የደም ናሙና በፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ተመራማሪዎች ያለምንም ሕጋዊ ፈቃድ ተወስዷል፡፡ ወጤቱ ከምን ደረሰ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሀገራቱም ‘‘በብሔራዊ ደኅንነት’’ ጭንብል ሸፍነው ይፋ አላደረጉትም፡፡ ይህም ጥቁሮችን እንደ ሸቀጥ እየተጠቀሙ የሚደረግ የዘርፉ ሕገ ወጥ ንግድ ነው፡፡

በ1996 (እ.አ.አ) በናይጀሪያ ካኖ ግዛት በተከሰተ ወረርሽኝ ፒፍዘር የተባለ የሕክምና የምርምር ተቋም ከሕሙማን ያለምንም ሕጋዊ ፈቃድ እና ዕውቅና የደም ናሙና ወሰደ፡፡ የኋላ ኋላ ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ለግዛቷ 75 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እና የደም ናሙናው ለተወሰደባቸው አራት ሕጻናት ቤተሰቦች የ175 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካሳ እንዲከፍል ቢወሰንም የድርጊቱ አስከፊ ጠባሳ ግን አሁንም ከጥቁሮች ልቡና አልተቀረፈም፡፡ በ1994 (እ.አ.አ) በዝምባቡዌ እና በ1900 (እ.አ.አ) አካባቢ በናሚቢያ መሰል ክብረ ነክ የሕክምና ምርምሮች በነጭ ተመራማሪዎች መካሄዳቸውን ላስተዋለ የአሁኑ የፈረንሳይ ተመራማሪዎች የክትባት እቅድ ምንጩ በቀላሉ ይገለፅለታል ነው ያለው ኖኮ በሐተታው፡፡

በ2011 የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን አሰማርቶ በፓኪስታን ሲያካሂድ የነበረው የሐሰት ክትባት የደም ምርምራ ዘመቻ ዓላማው የኦሳማ ቢን ላደን የዘረ-መል ምርምር ዘመቻ አካል መሆኑን ላወቀ ደግሞ ከሰሞኑ የከፉ ድርጊቶች ማለፋቸውን መረዳት እንደሚችል ዘገባው አስገንዝቧል፡፡

ምንጭ፡- አልጀዚራ

በታዘብ አራጋው

Previous articleበአሜሪካ ችካጎ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ከሞቱት አብዛኞቹ ጥቁሮች ናቸው ተባለ፡፡
Next articleየኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከወሎ ዩኒቨርሲቲና በአካባቢው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር በመሆን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየሠራ መሆኑ ተገለጸ::