
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት ተባብሶ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ምዕመናን ከሃይማኖት አባቶችና ከመንግሥት የሚተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማሳወቋ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ መመሪያውን የመተግበር ውስንነት እንዳለ አብመድ ትናንት በባሕር ዳር ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲናት ባደረገው ቅኝት ተመልክቷል፡፡ መመሪያው ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ምን መሠራት እንዳለበትም ከሃይማኖት አባት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ በአብያተ ክርስቲያናትና የአብነት ትምህርት ቦታዎች መተፋፈግ እንዳይኖር ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ ይህን የሚከታተል እስከ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ድረስ የተዋቀረ ግብረ ኃይል መቋቋሙንም አስረድተዋል፡፡ ከ6ሺህ በላይ የአብነት ተማሪዎችም ወደ ቤተሰቦቻቸው ተመልሰው አስቸጋሪውን ወቅት እንዲያሳልፉ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጅ መመሪያው ተግባራዊ የተደረገበት ጊዜ አጭር በመሆኑና በሁኔታዎች አለመመቻቸት ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው ያልሄዱ 1 ሺህ 459 የአብነት ተማሪዎች በሀገረ ስብከቱ መኖራውንም ጠቁመዋል፡፡ የአብነት ተማሪዎቹ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ቤተ ክርስቲያኒቱ እየሠራች ትገኛለችም ተብሏል፡፡
በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃም ይሁን በሊቃውንት ጉባኤ ተወስኖ በሀገረ ስብከት ደረጃ በተነገረው መመሪያ መሠረት በርካታ ምዕመናን ቤታቸው ውስጥ ሆነው እየጸለዩ እንደሚገኑም የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ መመሪያውን ተግባራዊ ያላደረጉ የሃይማኖቱ ተከታዮች እስከ ትናንት መጋቢት 27/2012 ዓ.ም ድረስ በጋራ ሆነውና ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ እንደነበር አንስተዋል፡፡ የሃይማኖቱ ተከታዮች የበሽታውን አሳሳቢነት አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያስተላለፈውን መመሪያ ማክበር እንደሚጠበቅባቸውም መክረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደተዘጋችና አገልግሎቱም እንደተቋረጠ ተደርጎ የሚሠራጨው ወሬም መታረም እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
የሲኖዶሱም ይሁን የመንግሥት መመሪያ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድተዘጋና አገልግሎቱ እንዲቋረጥ አለመሆኑን ነው የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውን ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ያስረዱት፡፡ የተላለፈው መመሪያ ቅዱስ ሲኖዶሱም፣ በየአብያተ ክርስቲያናት የሚመደቡ አገልጋይ ካህናትም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ አስፈላጊው ነገር ተዘጋጅቶላቸው ሱባኤ ይዘው፣ ጸሎት እያደረጉ አገልግሎቱን እንዲሰጡ መደረጉን ነው ያስገነዘቡት፡፡
ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደተዘጋች አድርገው የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሠራጨት ሕዝቡን የሚያደናግሩ ሰዎች እንዳሉ መታዘባቸውንም አንስተዋል፤ የሃይማኖቱ ተከታች የሚናፈሱ ወሬዎች ውሸት መሆናቸውን በመረዳት የተላለፈውን የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ማክበር እንዳለባቸው ነው ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ መልአክ ያሳሰቡት፡፡ ‘‘ሰዎች በቤት ውስጥ ጸሎት እንዲያደርሱ የተደረገበት ዓላማ የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ ነው’’ ያሉት የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውን ጉባኤ ሰብሳቢ በጋራ የሚደረጉ እንደ ድግስ፣ ሐዘንና መሠል ማኅበራዊ ክዋኔዎች የቫይረሱን መስፋፋት ሊያሰፉ ስለሚችሉ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበትም መክረዋል፡፡ አንድ ሰው ዝክር እንዲዘክር ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ የሚያዝዘው ድሆችና ጦም አዳሪዎችን ለማስታወስ እንጅ ከጎረቤቱ ጋር ብድር ሊመላለስበት እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የሃይማኖቱ ተከታዮች አጋጣሚውን ተጠቅመው ምፅዋቱን ማድረስ እንዳለባቸው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ