የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመኾን የምታደርገውን ድርድር የሚያፋጥን እንደኾነ ተገለጸ፡፡

10

ባሕር ዳር: ነሐሴ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመኾን የምታደገውን ሂደት የሚያፋጥን መኾኑን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ.ር) ገልጸዋል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ.ር) ከዓለም የንግድ ድርጅት አክሴሽን ዲቪዥን ዋና ዳይሬክተር ማይካ ኦሺካዋ ጋር ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት የድርደር ሂደትን አስመልክቶ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመኾን ጥያቄ ካቀረበች ረዥም ጊዜ ያስቆጠረች መኾኑን ገልጸው መንግሥት አሁን ላይ እየተገበረቻቸው ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የድርድር ሂደቱን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚያግዝ ነው ያስገነዘቡት።

በቀጣይ ለሚካሄደው 5ኛው የሥራ ቡድን ሥብሠባ ላይ የሚቀርቡ ሰነዶች ወደ ተግባር የገቡ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ያካተተ እንዲኾን ከድርጅቱ ባለሙያዎች ጋር ሰነድ በመከለስ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

የዓለም የንግድ ድርጅት አክሴሽን ዲቪዥን ዋና ዳይሬክተር የኢትዮጵያ የአባልነት ጥያቄን ካጓተቱ ምክንያቶች መካከል በቅርቡ ተግባራዊ መኾን የጀመሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መኾናቸውን ጠቅሰው ማሻሻያው የድርድር ሂደቱን እንደሚያፋጥን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት ያለ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ሙሉ አይኾንም ያሉት ዳይሬክተሯ ድርድሩን በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ድርጅቱ ቴክኒካል ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፍልሰታ ሕጻናቱ የሚናፍቋት፤ በጉጉት የሚጠብቋት”
Next article“የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና ታሪኩን ጠብቆ የሚሠራ ነው” የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን