
ባሕር ዳር: ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አዕምሮ የሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ሚዛን ማስጠበቂያ እና መቆጣጠሪያ ትልቁ ክፍል ነው። አዕምሮ ሲታወክ ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ይናጋሉ። የአዕምሮን ጤና መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ እንደኾነም የሥነ አዕምሮ ሀኪሞች ይመክራሉ።
በየአካባቢያችን የሥነ አዕምሮ እክል ከኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ ጋር ተዳምሮ የሥነ አዕምሮ ህመም የገጠማቸው በርካቶች በየቤቱ በሰንሰለት አልያም በገመድ ታስረው ወይም ቤት ተዘግቶባቸው አለፍ ሲልም ከማኅበረሰቡ ተገልለው በየጎዳናው ጨርቃቸውን ጥለው ተጎሳቁለው ይታያሉ። አቶ ወርቁ እጅጉ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ናቸው። የሥነ አዕምሮ ህመምን በተመለከተ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ እንደኾነ ጠቅሰው በዘርፉ ሊሠራበት እንደሚገባ ነው የነገሩን።
“የሚያብደው እና የሚሞተው አይታወቅም” የሚባል ዘመንን የተሻገረ አባባል እንዳለ የሚገልጹት አቶ ወርቁ ኅብረተሰቡ ህመሙ በባለሙያ የሚታከም እና የሚድን መኾኑን ተረድቶ ከማገዝ ይልቅ “ሰይጣን ነው፤ ልክፍት ነው” ወዘተ እያሉ ወደ ባሕላዊ ህክምና እየሄዱ ሳይንሳዊ ህክምናው ቸል እየተባለ ባለማወቅ ችግሩ እንዲባባስ ሲደረግ እንደሚመለከቱም ያስረዳሉ።
ከዚህ ባለፈም የሥነ አዕምሮ ህመም የገጠማቸውን ሰዎች ወደ ህክምና ወስዶ ከማገዝ ይልቅ ያልተገባ ስያሜን በመስጠት እንዲገለሉ እና ችግሩ እንዲባባስ እየተደረገ ነው የሚሉት አቶ ወርቁ ኅብረተሰቡንም ስለ አዕምሮ ጤና በስፋት ማስተማር ያስፈልጋል፤ መንግሥትም ለአዕምሮ ጤና ትኩረት ቢሰጥ ጥሩ ነው ሲሉም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።
በባሕር ዳር ፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሥነ አዕምሮ ህክምና ክፍል ኀላፊ ዶክተር ማቴዎስ ማሳኔ አዕምሮ ሥራው በአግባቡ ማሰብ፤ ስሜትን በልክ መምራት እና ባህሪን ማሥተዳደር እንደኾነ በመጥቀስ እነዚህን በትክክል መምራት ሲቸግር የአዕምሮ እክል አለ ብሎ መናገር እንደሚቻል ያስረዳሉ።
በባሕር ዳር እና አካባቢዋ ወደ ፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚመጡ የሥነ አዕምሮ ታካሚዎች መካከል 25 በመቶው አሳሳቢው “እስኪዞፍሬኒያ” የተባለው የሥነ አዕምሮ ህመም እንዳለባቸውም ዶክተር ማቴዎስ ይገልጻሉ። በዓለም አቀፍ ጥናቶች እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ቡታጅራ አካባቢ በተሠራ ጥናት ከ1 በመቶ በላይ “እስኪዞፍሬኒያ” በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዳለ ያመለክታል የሚሉን ዶክተር ማቴዎስ ይሄ ማለት ከ120 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግሩ አለ ማለት ነው ያላሉ።
በርካታ የሥነ አዕምሮ ህመሞች ቢኖሩም አሁን ላይ በፈለገ ሕይዎት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ወስጥ ከሚታከሙት የሥነ አዕምሮ ታካሚዎች መካከል 25 በመቶ የሚኾኑት “እስኪዞፍሬኒያ” እንደኾነም የሥነ አዕምሮ ስፔሻሊስት ዶክተር ማቴዎስ ያስረዳሉ። ይህ ማለት ደግሞ እስኪዞፍሪኒያ የተባለው የሥነ አዕምሮ እክል ምን ያህል አሳሳቢ እንደኾነም ጉልህ ማሳያ ነው ይላሉ።
“እስኪዞፍሬኒያ” የተባለው የሥነ አዕምሮ እክል መንስኤው ይሄ ነው ተብሎ መናገር የሚያስቸግር ቢኾንም በዘር እና ከአጋላጭ ሁኔታዎች ጋር ተደማምሮ የሚከሰት እንደኾነም ይገልጻሉ። አንዳንዴም በወሊድ (በምጥ) ጊዜ የሚፈጠሩ አደጋዎች፤ አፈጣጠር ላይ ጭንቅላት ውስጥ ያሉ ነርቮች ሲዛቡ እንዲሁም ጭንቅላት ላይ የደረሰ አደጋ ከሁኔታዎች ጋር ተደማምረው ለችግሩ ሊያጋልጡ እንደሚችሉም ዶክተሩ ያስረዳሉ።
የ”እስኪዞፍሬኒያ” ምልክቶቹ ያለው ዕውነታ ተገልብጦ መታየት፤ የሌለ ነገር መታየት፤ ሰው ሳይጠራቸው አቤት ማለት፤ ሰው ሳያወራቸው ያወራቸው መምሰል፤ የሌለውን ነገር ማየት፤ የሌለ ድምጽ ለእነሱ ብቻ መሰማት፤ የሌለ ድምጽን ማናገር፤ የተለየ ዕምነት መያዝ፤ የሚጠቅማቸውን ሰዎች እንደሚጎዷቸው ማሰብ፤ አብዝቶ መጠራጠር፤ ሰዎች ይከታተሉኛል፤ ካሜራ ገጥመውብኛል በማለት የሚረዷቸውን ሰዎች በሌለ ነገር መክሰስ፤ መሸሽ፤ መለፍለፍ፤ ብቻን ወጥቶ መሄድ፤ መፍራት እንደኾኑ አስገንዝበዋል። እየከፋ ሲሄድ ደግሞ መገለል፣ ስሜት አልባ መኾን እና አለማውራትም ሊከሰት እንደሚችል ዶክተር ማቴዎስ ያስረዳሉ።
እንደ ሥነ አዕምሮ ስፔሻሊስቱ ዶክተር ማቴዎስ አስተያየት “እስኪዞፍሬኒያ” በክትባት መልክ ቀድሞ መከላከል ባይቻልም አስቀድሞ የሥነ አዕምሮ ሀኪሞችን በማማከር እና በሳይንስ የተረጋገጡ የሥነ ልቦና ልምምዶችን በመውሰድ ጤናማ የሥነ አዕምሮ ሕይዎትን መምራት ይቻላል። ችግሩ ከተከሰተ በኃላ ግን እንደማንኛውም ህመም የሚታከም እንደኾነ ኅብረተሰቡ ተገንዝቦ ህክምናውን በሚገባ መከታተል እንዳለበት ዶክተሩ በአጽዕኖት ይመክራሉ።
ችግሩ ከተከሰተ በኃላ ግን “በባዮሳይኮሶሻል” በሚባል ሞዴል ህክምናው ይሰጣል የሚሉን ዶክተሩ ‘ባዮ’ ማለት መድኃኒቶችን በመስጠት ህክምና ማድረግን የሚገልጽ ሲኾን ‘ሳይኮ’ ሥነ ልቦናዊ የንግግር እና የምክክር ህክምናን ያሳያል። ‘ሶሻል’ የሚለው ደግሞ ከማኅበረሰቡ የሚደረግ ድጋፍ እና ክትትልን የሚያሳይ ሲኾን መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ህክምናዎችንም የህመሙን መንስኤ እና ምክንያት ባገናዘበ መንገድ ችግሩ የገጠማቸውን ሰዎች ማገዝ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው።
በአጠቃላይ ግን ችግሩ የገጠማቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ህክምና ማዕከል መጥተው በመታከም መፍትሄ ማግኘት እንደሚችሉ ዶክተር ማቴዎስ በአጽዕኖት ይገልጻሉ። ከዚህ ባለፈም ዶክተር ማቴዎስ “ኩላሊቱ የታመመን ሰው ኩላሊቱ ታመመ፤ ዐይኑን የታመመውን ሰው ዐይኑ ታመመ ከተባለ አዕምሮውን የታመመ ሰውም አዕምሮውን ታመመ እንጅ ቀውስ፣ እብድ እና መሰል ያልተገቡ ስያሜዎችን መስጠት ችግሩን የሚያባብስ በመኾኑ ኅብረተሰቡ ከዚህ ያልተገባ ስያሜ ሊቆጠብ ይገባል” ሲሉም ይመክራሉ።
ዶክተር ማቴዎስ በሥራ ላይ የገጠማቸውን ሲገልጹም “የሥነ አዕምሮ ታካሚዎች ከድብደባ ብዛት ጆሯቸው የማይሰማ፤ ከጠንካራ የሰንሰለት እስራት ብዛት የእጅ እና የእግር አጥንቶቻቸው የተሰበረ እንዲሁም ሌሎች ልብ የሚሰብሩ መሰል ጉዳቶች ገጥመዋቸው እንደሚመጡ ይገልጻሉ። ይህ ሁኔታም ችግሩን የሚያባብስ በመኾኑ ኅብረተሰቡ የሥነ አዕምሮ ታካሚዎችን ተንከባክቦ ወደ ህክምና በማድረስ በኩል ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባውም ዶክተሩ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ግርማ ሙሉጌታ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!