ከ641 ሺህ ኩንታል በላይ የጥጥ ምርት ለመሠብሰብ እየሠራ መኾኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

18

ባሕር ዳር: ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በመምሪያው የሰብል ልማት እና ጥበቃ ባለሙያው አቶ ደግሰው አየለ አካባቢው ለጥጥ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ልማቱ መስፋፋቱን ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮው የክረምት ወቅት የጥጥ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግ ከ800 ኩንታል በላይ የተላጨና በኬሚካል የታሸ የጥጥ ዘር በማቅረብ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉንም ገልፀዋል።

በመተማ፣ ቋራ እና ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳዎች ከለማው ከ23 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ ከ12 ሺህ 200 ሄክታር በላይ የሚኾነው በባለሃብቶች የለማ ጥጥ መኾኑን ተናግረዋል። በጥጥ ልማቱ 4 ሺህ 150 የሚኾኑ አርሶ አደሮች እና 242 ባለሃብቶች ተሳታፊ መኾናቸውንም አመልክተዋል።
የጥጥ ምርታማነትን ለማሳደግም ከተሻሻለ ዘር አቅርቦት ባሻገር እስከ ሁለት ዙር ድረስ ደጋግሞ የማረም አሠራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ባለሙያው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችን ፍላጎት ለማሟላት የአየር ንብረቱ ተስማሚ በኾኑ ወረዳዎች ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እየተተገበረ እንደሚገኝም አብራርተዋል። በመኸር ከለማው የጥጥ ምርትም ከ641 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ምርቱም በገንደ ውኃ ከተማ ለሚገኙ ሦስት የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካዎች ገበያ ትሥሥር በመፍጠር አምራች ባለሃብቶች እና አርሶ አደሮች ለምርታቸው ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ የሚያስችል መኾኑን አስረድተዋል። በመተማ ወረዳ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር እሸቱ አምባው ባለፈው ዓመት የጥጥ ገበያ በመሻሻሉ በዚህ ዓመት ከአራት ሄክታር በላይ መሬት በጥጥ ማልማት ችለዋል።

በጥጥ ካለሙት መሬትም ከ80 ኩንታል በላይ ምርት በማግኘት ገቢያቸውን ለማሻሻል እንዳሰቡም ተናግረዋል። በዚሁ ወረዳ በእርሻ ሥራ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ዳዊት ውለታው በበኩላቸው በዚህ ዓመት 40 ሄክታር መሬት በጥጥ ማልማት ችለዋል። ባለ ሃብቱ በአሁኑ ወቅት የአረም እና ተባይ ክትትል እና ቁጥጥር እያደረጉ ሲኾን የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፈው የምርት ዘመን በጥጥ ከለማው ከ335 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል ሲል የዘገበዉ ኢዜአ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“እየተከልን እናንብብ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleከሕገወጥ ነጋዴዎች የተወረሰ 800 ሺህ ሊትር ዘይት ተከፋፈለ፡፡