
ባሕር ዳር: ነሐሴ 02/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቡና ውስጥ ያለው አነቃቂ ንጥረ-ነገር ካፌን ይባላል። ቡና በዓለማችን ካሉ እጅግ አነቃቂ እና በርካታ ተጠቃሚ ያለው ምርት እንደኾነም ይነገራል። ኢትዮጵያ ቡናን በማምረት እና ወደ ውጭ በመላክ ከፍ ያለ ስም ያላት ሀገር ናት፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አትክልት እና ፍራፍሬ የመስኖ ዉኃ አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድም እንደሚናገሩት በአማራ ክልልም ቡናን በሰፊው የማምረት ጸጋ አለ፡፡ በተለይ በዘጌ፣ በጎንደር ዙሪያ፣ በጃቢ ጠህናን እንዲሁም በምስራቅ አማራ ክፍል አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ቆየት ያለ ቡናን የማልማት ልምምድ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡
አቶ ይበልጣል የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንደሚናገሩት በከፍተኛ እና በመካከለኛዉ የአማራ ክልል 350 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና መልማት ይቻላል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ቡናን በተሻለ መንገድ ለማምረት በክልሉ 21 ሺህ 457 ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍኗል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ በመስኖ 12 ሺህ 831 ሄክታር ከመስኖ ውጭ 2 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ቡና አሁን ምርት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
በክልሉ መልማት ከሚችለው 350 ሺህ ሄክትር መሬትውስጥ የለማዉ 21 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ ነዉ ያሉት አቶ ይበልጣል ካለዉ የመልማት አቅም አንጻር ሲታይ ይህ ዝቅተኛ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ወደፊት ቡናን በተለየ መልኩ ለማምረት የክልሉ መንግሥት ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት ማምረት ድረስ የበጀት ድጋፍ እያደርገ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ በዚህም በክልሉ ከ2 እስከ 3 ሺህ ሄክታር በሚኾን መሬት ላይ በየዓመቱ ወደ 9 ሚሊየን ቡና ይተከላል፡፡
አቶ ይበልጣል ቡና ከፍተኛ የኾነ የገንዘብ ወጭ የሚጠይቅ ሥራ ነው ይላሉ፡፡ አንድ የቡና ተክልን ለማዘጋጀት ከ10 እስከ 15 ብር ሊደርስ የሚችል ወጭ እንደሚፈልግ ያስረዳሉ፡፡ በዓመት 9 ሚሊየን ቡና ለመትከል ከ100 አስከ 150 ሚሊየን የሚኾን የገንዘብ ወጭ እንደሚጠይቅም ነዉ የገለጹት፡፡
ምርቱን በስፋት ለማምረት 21 የተመረጡ ወረዳዎች ላይ ሥልጠና በመስጠት፣ ዝርያን በመምረጥ እንዲሁም ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ምርታማነትን ለመጨመር እየተሠራ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በበጀት ዓመቱ 76 ሺህ 659 ኩንታል በመስኖ የቡና ምርት ተመርቷል ብለዋል፡፡
አቶ ይበልጣል አክለዉም ቡናን ከሌሎች ምርቶች ጋር ደርቦ ሳይኾን ብቻዉን አደረጃጀት በመፍጠር መደገፍ ይገባል ይላሉ፡፡ አቅም ያላቸዉ ባለሀብቶች ወደ ሥራዉ እንዲገቡ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!