
ባሕር ዳር: ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሀገራችን የሰው ሠራሽ አስተውሎት መተዋወቅ ከጀመረበት ቅርብ ዓመታት ጀምሮ ማሽን ለርኒንግ ወይም በመማር ራሱን የሚያበቃ ማሽን የሚለው ጽንስ ሃሳብ እየተለመደ መጥቷል።
ማሽን ለርኒንግ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ንዑስ ክፍል ሲኾን ከሚሰጠው መረጃ በመማር ራሱን ማብቃት የሚችል የኮምፒውተር ሥርዓት ለማልማት የሚያገለግል ነው። የመማር ሂደቱ ቀስ በቀስ ተግባራትን በተሻለ ሁኔታ ለመፈጸም እስከ መቻል የሚመጣ ነው።
በመረጃዎች ውስጥ ያለውን ግንኙነት እና ቅርጽ ለመለየት የሚያግዙ የማሽን ለርኒንግ ስልተ-ቀመሮች ወይም አልጎሪዝሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ። በልምምድ ውስጥ የተገኙትን የመረጃ ግብዓቶች እንደ መነሻ በመውሰድ ስልተ- ቀመሮቹ ተግባራትን ያከናውናሉ።
በማሽን ለርኒንግ ሂደት የሚከናወኑ ተግባራት ያለፈውን መረጃ በመጠቀም የወደፊቱን መተንበይ፣ መረጃን በመደብ ማደራጀት፣ የይዘት ጭብጥ ለይቶ ማውጣት እንዲሁም አዲስ ይዘት ማመንጨት ሊኾኑ ይችላሉ።
አዲስ መረጃን ማመንጨትን የሚሠሩ ጀነሬቲቭ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች ሲኾኑ ለአብነት የኦፕን ኤ. አዩ ቻት ጂፒቲ፣ የጉግሉ ጀሚናይ እና የማይክሮ ሶፋቱ ከኦፓይሌት ይጠቀሳሉ።
የማሽን ለርኒንግ ሂደትን በመጠቀም ሰዎች እንዲፈጠርላቸው የሚፈልጉትን ይዘት ማመንጨት ይችላሉ። የምንፈልገውን ምስል፣ የምንፈልገውን የሥነ ጽሑፍ ዓይነት እንዲሁም የጥናት ውጤቶችን ማመንጫት ይችላል።
ማሽን ለርኒንግ በበርካታ ዘርፎች እየተተገበረ ያለ ሲኾን በሳይበር ንግድ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እና መሰል ግንኙነቶች የደንበኛን ነባር ባሕርይ በማጥናት ይዘቶችን እንዲመለከቱ፣ እንዲገዙ እና ስሜታቸውን እንዲገልጹ የሚያደርግ መረጃን በማቅረብ ተጽዕኖን ይፈጥራል።
በሰው አልባ መኪኖች ላይ ደኀንነቱ የተጠበቀን መንገድ ለመምረጥ ጥቅሙ የጎላ ነው። በሕክምናው ዘርፍም ለምርመራ እና ቀጣይ ለሚኖር የሕክምና እቅድ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል።
ሌላው እና የተለመደ የሚባለው የማሽን ለርኒንግ ጥቅም የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመለየት፣ የሳይበር አጭበርባሪዎችን ጥቃት ለመከላከል፣ ጎጂ መተግበሪያዎችን ቀድሞ ለማወቅ እና ሌሎች ይጠቀሳሉ።
ማሽን ለርኒንግ ችግርን ለመፍታት በጣም ጉልበታም የሚባል የሰው ሠራሽ አስተውሎት ንዑስ ክፍል ቢኾንም ብቁ ባለሙያ እና ጠቃሚ መረጃዎችን ይፈልጋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!