
ባሕር ዳር: ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው የ2016 ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 ዕቅድ ትውውቅ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ አካሄዷል። በውይይቱ ላይ የቢሮው ኀላፊ እንድሪስ አብዱ እንዳሉት በ2016 በጀት ዓመት ባለሃብቶች ክልሉ በገጠመው ወቅታዊ ችግር ተደናግጠው ለቅቀው እንዳይወጡ በማግባባት ምርት እንዳይቋረጥ ተደርጓል ብለዋል።
አዳዲስ ባለሃብቶችም ወደ ክልሉ እንዲመጡ እና ኢንቨስት እንዲያደርጉ መሠራቱን አቶ እንድሪስ ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ 437 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 2 ሺህ 650 ባለሐብቶች የሚኾኑ ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎንችን ክልሉ ተቀብሎ ማስተናገዱን እና ወደ ሥራ እንዲገቡም መሠራቱን ነው ቢሮ ኀላፊው የገለጹት።
ኀላፊው 38 የሚኾኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች 137 ሺህ ቶን ምርት አምርተው ወደ ውጭ ሀገር በመላክም ከ134 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል። ክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግርም ውድመት ደርሶባቸው የነበሩ የአበባ ልማቶች የነበረውን ፈተና ተቋቁመው ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዳስገኙ ነው አቶ እንድሪስ የተናገሩት።
በአማራ ክልል በ2016 በጀት ዓመት በጠቅላላ ከ149 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት መቻሉን ነው ኀላፊው የገለጹት። እንደ ቢሮ ኀላፊው በጸጥታው ችግር ምክንያት ሸቀጣ ሸቀጥ ከመሐል ሀገር ወደ አማራ ክልል የተገደበ በመኾኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ባላቸው ጥሬ ዕቃ በማምረት በየአካባቢው ገበያውን በማርገብ አወንታዊ ሚና ተጫውተዋል።
በዚህም 564 ሺህ ቶን በማምረት መንግሥት ለውጭ ሀገር ምርት ሊያወጣ የነበረውን 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል። ለ44ሺህ 102 ዜጎችም ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም በዘርፉ ያለውን ማነቆ በመፍታት እና ባለድርሻዎችን በማገናኘት ከ218 በላይ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ የነበረው አበርክቶ ጉልህ ነው ሲሉ አቶ እንድሪስ ጠቁመዋል።
የቢሮ ኀላፊው በ2016 በጀት ዓመት የአገልግሎት አሰጣጡ አሁንም አልሚውን ያረካ አለመኾኑን በችግርነት አንስተዋል። ዘርፉ ከደላላ እና ከሌሎችም ንክኪዎች ነጻ እንዲኾን ተቆራርጦ መሥራት እንደ ሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። አሠራሩን በዲጂታላይዜሽን አዘምኖ መከናዎን አንዳለበትም ነው የተናገሩት።
የአዲስ አልሚዎችን ጥያቄ በማስተናገድ ከዚህ በፊት ተላልፎ የተሰጠ እና ለረጅም ጊዜ ታጥሮ የተቀመጠን መሬት ወደ ሥራ ለማስገባትም እርምጃ መወሰድ ይገባል ነው ያሉት።
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እሸቱ አሊ መርሻ እንዳሉት በ28 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 4 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል። ከ2017 ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገባ ከ82 ሄክታር በላይ መሬት በፓርክ ደረጃ እንደተካለለም ነው የጠቆሙት።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማዬ ልጃለም ደግሞ ባለሃብት በመሳብ እና መሬት በማቅረብ ረገድ አበረታች ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት። በ2016 ዓ.ም ለ350 ባለሃብቶችም የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠታቸውን ለአብነት አንስተዋል። የእነዚህ ባለሃብቶች ካፒታልም ከ116 ቢሊዮን ብር በላይ እንደኾነም ነው መምሪያ ኀላፊው የገለጹት።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!