
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የኢትዮጵያ ባንኮች ህልውናን ያስቀጠለ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ዝግ አድርጋ መቆየቷ ለዘመናት ፈተና ውስጥ እንድትወድቅ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ ለአብነትም የወጪ ንግዱ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሬ ማስገባት ተስኖት መቆየቱን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ምርቶችም በኮንትሮባንድ እንዲወጡ ማድረጉን ነው ያነሱት፡፡
ኢትዮጵያ ባላት አቅም ልክ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ መኾን እንዳልቻለችም ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል የጥቁር ገበያ ሥርዓት እንዲስፋፋ በማድረግ የዋጋ ንረት በዜጎች ላይ ጫና እንዲፈጥር ማድረጉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ ከዚህ አኳያ ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ የተጫኑ ስብራቶችን በማንሳት የተሻለ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡ በተለይ የፋይናንስ ሴክተሩን ህልውና በማስቀጠል ረገድም ሚናው የጎላ መኾኑን አብራርተዋል፡፡
ለአብነትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቦንድ ግዥ ያሠባሠበውን ገንዘብ ብድራቸውን መመለስ ላልቻሉ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ ይህም ባንኩን ባለ እዳ እንደሚያደርገው እና እዳውን መመለስ ካልቻለ ደግሞ መፍረሱ አይቀሬ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መፍረስ ኢትዮጵያውያን በባንኮች ላይ ያላቸውን እምነት እንደሚያሳጣ ጠቁመዋል፡፡
ይህም የሀገር ውስጥ ባንኮችን በገበያው የመቀጠል ዕድላቸውን አዳጋች ያደርገው እንደነበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) እና ከዓለም ባንክ ጋር ባደረጋቸው ድርድሮች ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚመለከት መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ በድርድሩም ባንኩ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚኾን ተጨማሪ ገንዘብ ከተቋማቱ ማግኘቱን አብራርተዋል፡፡
እንደ ኢዜአ ዘገባ ይህም የባንኩን ህልውና ያስቀጠለ ከመኾኑም በላይ በኢትዮጵያ ልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ ይበልጥ እንደሚያስቀጥልም ተናግረዋል፡፡